Fana: At a Speed of Life!

የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ አደረጉ።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ከነዋሪዎቹ የተበረከቱ ድጋፎችን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ሚኒስቴር ዴኤታ ለወይዘሮ ማርታ ሎጂ አስረክበዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት አቶ መለሰ ዓለሙ እንደገለጹት የተጀመረው ሀገራዊ ሉዓላዊነትን የማስጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ስራ አጠናክረን መቀጠል የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል።

በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣው ጥቃት በሁላችንም ላይ የተፈጸመ ነው ያሉት ኃላፊው በተለይም የትግራይ ህዝብ ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች የተለየ ጥቅም የማይፈልግ እና ለሀገር ልማት እና እድገት የሚተጋ ሲሆን የትግራይ ተወላጅ የሆኑትን የከተማችን ነዋሪዎች በተለየ መልኩ ማየት የለብንም ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም የከተማው ነዋሪዎችም የከተማዋን ሰላም ለመጠበቅ በሚያደርጉት አስተዋጽዖ በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ መለሰ  አሁንም በንቃት የአከባቢን ሰላም መጠበቅ የሁልጊዜ ተግባር እና የሁሉም ድርሻ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

ኃላፊው “ይህን ስግብግብ ጁንታ ለአንዴና ለመጨረሻ በመገላገል የኢትዮያን ብልፅግና ለማረጋገጥ እንረባረብ” ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.