Fana: At a Speed of Life!

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለ500 አርሶ አደሮች የተሻሻሉ የምርጥ ዘር ዝርያዎችን አከፋፈለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለ500 አርሶ አደሮች  የተሻሻሉ የምርጥ ዘር ዝርያዎችን ማከፋፈሉን አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምርምር ጉዳዮች ሃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ለማ÷ምርጥ ዘሮቹ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው የቦሎቄ፣ በቆሎና ድንች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተሻሻሉ ዝርያዎቹ በሐረማያ ወረዳ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 500 አርሶአደሮች የተከፋፈሉ ሲሆን÷ ዩኒቨርሲቲው የአርሶአደሩን ኑሮ የሚያሻሽሉ ሰብሎችን በምርምር በማውጣት ላይ እንደሚገኝ ሃላፊው ጠቁመዋል።

እነዚህ ሰብሎችም ምስራቅ ሐረርጌን ጨምሮ ሱማሌና ሐረሪ ክልሎችን እንዲሁም በድሬደዋ አስተዳደር የሚገኙ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት፡፡

ዛሬ የተከፋፈሉት ምርጥ ዘሮች ባለፈው በጋ ግብርና ባጋጠመው ድርቅ ምክንያት መድረስ ያልቻለውን ምርት ለማካካስ ያስችላል ብለዋል።

የሐረማያ ወረዳ የግብርና ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሹኩሪ መሀመድ በበኩላቸው÷ የአርሶአደሩን ህይወት ለመቀየር ዩኒቨርሲቲው እየሰራ ያለውን ስራ ጽህፈት ቤታቸው እንደሚያግዝ አረጋግጠዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያከፋፈላቸው ምርጥ ዘሮች በአጭር ጊዜ የሚደርሱ እና በሽታን መቋቋም የሚችሉ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በእዮናዳብ አንዱዓለም

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.