Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመደበኛ ስብሰባው የሚኒስትሮች ምክር በትግራይ ክልል ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፀደቀ።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መሰብሰቢያ አደራሽ አካሂዷል።

በመደበኛ ስብሰባውም በኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመቀበልና ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ተመልክቷል።

ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላም የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በትናትናው እለት ባደረገው 21ኛ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ፥ በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ በተለይም የሀገርን ሉዐላዊነት የሚገዳደሩ፣ የፌደራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በክልሉ እንዳይወጣ እና ሀገሪቷን የጦር አውድማ የሚያደርጉ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎችን ጭምር በመጣስ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈፀሙ በመሆኑ፤ ይህን ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን በመረዳት፤ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ እና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን በመቆጣጠር በሀገሪቱ ሰላምና ሕልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ መከላከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት የሚከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለ6 ወራት ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተውጣጡ አባላት ያሉት ግብረኃይል በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።

ግብረኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን ‘‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሀይል’’ ተብሎ እንደሚጠራም ተነግሯል።

አዋጁ በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ተፈፃሚ የሚደረግ ሲሆን፣ እንደ አስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ ወይም ቀሪ የሚሆንባቸውን ተጨማሪ አካባቢዎችን ግብረኃይሉ በሚያወጣው በመመሪያ ይወስናል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎች በየጊዜው ለህብረተሰቡ የሚሰጡ ይሆናል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.