Fana: At a Speed of Life!

የሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያና የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በብሪታንያ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “የሕዳሴ ግድብ የሀገር ልማት እና ዕድገት ተስፋ” በሚል መሪ ቃል በዩናይትድ ኪንግደምና አየርላንድ ለሁለት ወራት የሚቆይ የገቢ ማሰባሰቢያ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በይፋ ተጀምሯል።

ንቅናቄውን የተጀመረው በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያውያን የእርቅ እና የሰላም ኅብረት ከDefend Ethiopia ግብረ ኃይል፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በአየርላንድ ከሚገኙ ሲቪል ማኅበራት እንዲሁም በለንደን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በንቅናቄው ማስጀመሪያ ላይ እንደተናገሩት የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ባሉ መላው ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እና ርብርብ እየተካሄደ ነው፡፡

“ግድቡ 60 በመቶ ለሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በማስገኘት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን ቁልፍ ሚና አለው” ብለዋል አምባሳደር ተፈሪ።

በዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በለንደን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዢ እና በልገሳ መልክ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አመልክተዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም እና በአየርላንድ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል የሚሸርቡትን ሴራ ለመመከት የሚያስችሉ ተግባራትን በትጋት በማከናወን ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ንቅናቄው በመጪው ክረምት ከሚካሄደው የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ጋር የተቀናጀ በመሆኑ፣ ዳያስፖራው ግድቡ በስኬት እንዲጠናቀቅ ሀገራዊ ኃላፊነት እና ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.