Fana: At a Speed of Life!

የሕግ ማስከበር ሥራውን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ማንኛውም ድርጊቶች ላይ የሕግ እርምጃ ይወሰዳል- የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕግ ማስከበር ሥራውን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ማንኛውም ድርጊቶች ላይ አስፈላጊውን የሕግ የማስከበር እርምጃ የሚወስድ መሆኑን የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ጸጥታ ምክር ቤት የክልሉን የሰላምና እና ደህንነት ሁኔታ በጥልቀት ከገመገመ በኋላ የአሸባሪው ህወሓት ወረራ ስጋትን ለመመከት ዝግጅት ማድረግ እና የክልሉን አንድነት የሚሸረሽሩ ሕገወጥ ተግባራትን ለማረም ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል፡፡
ሕግ የማስከበር ሥራውን በአጭር ጊዜ እና በዝቅተኛ ጉዳት ለማጠናቀቅ መላው የጸጥታ መዋቅር ከሰላም ወዳዱ ሕዝብ ጋር በጋራ እየሠራ በሚገኝበት ወቅት ፈቃድ ያላገኘ ሰልፍም ሆነ የጎዳና ላይ ትዕይንት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገልጿል፡፡
በዚህ ድርጊት ላይ በቅስቀሳ እና አመጽ ጥሪ በሚያቀርቡ አካላት ላይ እንዲሁም በሰልፍ ሰበብ የሕግ ማስከበር ሥራውን ለማደናቀፍ በሚደረጉ ማንኛውም ድርጊቶች ላይ አስፈላጊውን የሕግ የማስከበር እርምጃ የሚወስድ መኾኑን ያሳውቃል።
የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጠው መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል:-
የአማራ ክልል ጸጥታ ምክር ቤት የክልሉን የሰላምና እና ደኅንነት ሁኔታ በጥልቀት ከገመገመ በኋላ የአሸባሪው ትህነግ ወረራ ስጋትን ለመመከት ዝግጅት ማድረግ እና የክልሉን አንድነት የሚሸረሽሩ ሕገወጥ ተግባራትን ማረም አስፈላጊ መኾኑን መወሰኑ ይታወሳል።
ሕግ የማስከበር ሥራው ዋና ዓላማ ሊቃጣ የሚችልን የአሸባሪው ትህነግ ድጋሚ ወረራ ለመቀልበስ፣ ለክልላችን ሕዝቦች ሰላም እና ደኅንነት ዋስትና ለመስጠት እንዲሁም የሚታየውን ሕገ ወጥነት መልክ በማስያዝ ሕዝቡ እየጠየቀ ያለውን የልማት እና መልካም አሥተዳደር ጥያቄ ለመፍታት ዓላማ ያደረገ እንደሆነ የክልላችን ርእሰ መሥተዳድር ለሕዝባችን መግለጻቸው ይታወሳል።
ካለፉት ቀናት ጀምሮ እየተከናወነ በሚገኘው ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠርጣሪዎች ያለምንም ግጭት እጃቸውን ለሕግ እንዲሰጡ የማድረግ እንዲሁም እጃቸውን በሰላም ለሕግ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጉዳት የመቀነስን ሥራ በመሥራት በሰላም ወዳዱ ሕዝባችን አጋርነት ሕግ የማስከበር ሥራውን እያከናወነ ይገኛል።
ይህ ሕግ የማስከር ሥራ ለሕዝባችን ሰላም እና ደኅንነት ለክልላችን እና ሀገራችን የሰላም ዋስትናን ዓላማ በማድረግ እየተከናወነ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከዋና ጠላቶችችን ጋር በማበር ክልላችንን እና ሀገራችንን ለማፍረስ የሚሠሩ አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ባለቤቶች እና ግለሰቦች በአንዳንድ የክልላችን አካባቢዎች ሰልፍ መጥራት እና ለሰላም ማስከብር ሥራው እንቅፋት የሆኑ ቅስቀሳዎችን እያደረጉ ይገኛሉ።
ነገር ግን በክልላችን የትኛውም አካባቢ ሕጋዊ ጥያቄ ያቀረበም ሆነ ፈቃድ ያገኘ ሰልፍ የለም።
ሕግ የማስከበር ሥራውን በአጭር ጊዜ እና በዝቅተኛ ጉዳት ለማጠናቀቅ መላው የጸጥታ መዋቅራችን ከሰላም ወዳዱ ሕዝባችን ጋር ሆኖ እየሠራ በሚገኝበት ወቅት እንዲህ አይነት ሕገወጥ ፈቃድ ያላገኘ ሰልፍም ሆነ የጎዳና ላይ ትዕይንት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ እየገለጸ በዚህ ድርጊት ላይ በቅስቀሳ እና አመጽ ጥሪ በሚያቀርቡ አካላት ላይ እንዲሁም በሰልፍ ሰበብ የሕግ ማስከበር ሥራውን ለማደናቀፍ በሚደረጉ ማንኛውም ድርጊቶች ላይ አስፈላጊውን የሕግ የማስከበር እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ያሳውቃል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.