Fana: At a Speed of Life!

የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የተሻለ የአመራር ስልጠና እንዲሰጥ የሚያደርጉ የሪፎርም ስራዎችን እያካሔደ መሆኑ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) አካዳሚው ኢትዮጵያ ካለችበት ለውጥ አንፃር መራመድ እንዲችል የሚያደርጉት የሪፎርም ስራዎች እያካሔደ መሆኑ ተገለፀ።

የአካዳሚውን ስያሜ ለመቀየር የሚያስችሉ ሕጋዊ አካሔዶችና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች መጀመራቸውም ተገልጿል።

አካዳሚው ለተለያዩ አመራሮች አካታች በሆነ መንገድ ስልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችለው ቅድመ ሁኔታዎችን ማጠናቀቁን አመልክቷል።

የአካዳሚው ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲና የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነሩ አቶ በዛብሕ ገብረየስ በአካዳሚው የተገነባውን አዲስና ዘመናዊ የማስተማሪያ ሕንፃ ጎብኝተዋል።

አቶ አወሉ አመራሩ በተደራጀ መንገድ ክሕሎትን እንዲላበስ ማድረግ በቀጣይ አገሪቱ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ ትልቁን መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

አካዳሚው ሲመሰረት ለገዥው ፓርቲ ብቻ እንዲያገለግል ተደርጎ የተዋቀረ ቢሆንም፤ አካሔዱን በመቀየር ሌሎች አካላትን አካቶ ሊሰራ የሚችልበት ሪፎርም መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

አካዳሚው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ሲያራምድ የነበረ ቢሆንም፤ አዲስ በተዘጋጀው ሪፎርም ግን ከአገሪቷ ለውጥ ጋር ሊያራምደው የሚችለው አወቃቀር እንዲከተል ተደርጓል ነው ያሉት።

ከዚህ ውስጥም ምሁራንን በማሳተፍና ጠንካራና መጠነ ሰፊ ሪፎርም በማዘጋጀት የአካዳሚውን ተልእኮ ፣ ስያሜና ዝርዝር ተግባራት በአዲስ መልክ እንዲቃኝ መደረጉን ገልፀዋል።

የአመራር ብቃት ማዕቀፍ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በማእቀፉም በየደረጃው ያሉ አመራሮች ብቃት የሚለካበት ስርአት የሚዘረጋ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አካዳሚው በአዲስ መልክ ያስገነባው ዘመናዊ ሕንፃ 95 በመቶ የተጠናቀቀ በመሆኑ በቀጣዩ ወር ተመርቆ ስራ እንደሚጀምርም ነው የገለጹት።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነሩ አቶ በዛብሕ ወልደየስ በበኩላቸው፤ አካዳሚው በአሁኑ ወቅት ራሱን ከአገሪቷ ለውጥ ጋር ለማራመድ እያካሔደው ያለው ተግባራት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

እስካሁን በኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደርና የፖለቲካ ስራ ተቀላቅሎ የቆየ በመሆኑ አካሔዳቸውና ተግባራቸው በውል የተለየ እንዳልነበር ጠቁመው፤ አካዳሚው የስራ መሪዎች ሊኖራቸው በሚገባ ብቃትና ክሕሎት ማላበስ ላይ አተኩሮ እንዲሰራ የሚያደርገው ተልዕኮ እንደተሰጠውም ነው የገለጹት።

አካዳሚው አመራሮችን በሁለተኛ ዲግሪ እና በዶክትሬት ዲግሪ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.