Fana: At a Speed of Life!

የመራጮች ምዝገባ ለሁለት ሳምንት ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የመራጮች ምዝገባ ለሁለት ሳምንታት መራዘሙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
የመራጮች ምዝገባ መራዘምን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃግብር መሰረት የመራጮች ምዝገባ ቀን ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ይታወቃል።
እስካሁን በተከናወነው የመራጮች ምዝገባ ሂደትም በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የምዝገባው ሂደቶች በተለያየ ደረጃ ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ለምሳሌ ያህልም በሶማሌ እና በአፋር ክልል የመራጮች ምዝገባ ዘግይቶ ሲጀመር በሌሎች ክልሎች ደግሞ ቀደም ብሎ ሲከናወን ቆይቷል።
የመራጮች ምዝገባ በቀደመው ሳምንት ቦርዱ ካሳወቀበት ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ የተሻሻለ ሲሆን የምርጫ ጣቢያዎች ያልተከፈቱባቸው የነበሩት የአፋር ብሔራዊ ክልል እና የሶማሌ ብሔራዊ ክልልም የምርጫ ጣቢዎች ተከፍተው የመራጮች ምዝገባን ማከናወን ጀምረዋል።
በጥቅሉ ሲታይም እስከ ትላትንና ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 18 ሚልዮን 427 ሺህ 239 ዜጎች የተመዘገቡ ሲሆን በ41,659 ምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን እየመዘገቡ ይገኛሉ።
ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ቀን ማጠናቀቂያ ዛሬ መሆኑን ተከትሎ የስራ ሂደቱን ያጋጠሙትን ችግሮች መርምሯል።
በዚህም መሰረት
1. የመራጮች ምዝገባ በግማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ዘግይቶ በመጀመሩ
2. በጊዜው በተጀመረባቸውም ቦታዎች የመራጮች ምዝገባ መረጃዎች እጦት እና በሌሎች ምክንያቶች ለመመዝገብ ጊዜ በመውሰዱ
3. የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቁ በቀሩት ጥቂት ቀናት በአንድ ምርጫ ጣቢያ 1500 ሰው ብቻ መመዝገብ በመቻሉ የተነሳ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በሚገኙ የተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ በመቋረጡ እና ተጨማሪ ምርጫ ጣቢያዎች በመክፈት ሂደት ክፍተት በመፈጠሩ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ እንዲራዘም ወስኗል።
በዚህም መሰረት
1. የመራጮች ምዝገባ እጅግ ዘግይቶ በጀመረባቸው በአፋር እና በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ ለሶስት ሳምንት ተራዝሟል ።
2. ይህም ማለት የመራጮች ምዝገባ ግንቦት 06 ቀን 2013 የሚጠናቀቅ ይሆናል ማለት ነው።
2. የመራጮች ምዝገባ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በተስተጓጎለባቸው ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለሁለት ሳምንት ተራዝሟል ይህም ማለት የመራጮች ምዝገባ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 የሚጠናቀቅ ይሆናል ማለት ነው።
3. የመራጮች ምዝገባ እስካሁን ባልተጀመረባቸው እና የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ የመራጮች ምዝገባን የማስጀመር እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል።
በነዚህ ዞኖች አሊቦ – ሆሮ ጉድሩ ፣ ኮምቦልቻ- ሆሮ ጉድሩ ፣ጊዳም – ሆሮ ጉድሩ ፣ አያና – ምስራቅ ወለጋ ፣ ገሊላ- ምስራቅ ወለጋ ፣ ቤጊ- ምእራብ ወለጋ ፣ ሰኞ ገበያ- ምእራብ ወለጋ የመራጮች ምዝገባ አሁንም የማይጀመር ሲሆን ከነዚህ ውጪ ባሉት ወረዳዎች የመራጮች ምዝገባን ለመጀመር የቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ እና የአስፈጻሚዎች ስልጠናንም እየተሰጠ ይገኛል።
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሽ ዞን ከሰጎን ወረዳ ውጪ የመራጮች ምዝገባን ለማካሄድ የቁሳቁስ ስርጭት እና የአስፈጻሚዎች ስልጠና እየተከናወነ ይገኛል።
በመሆኑም በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን እንዲሁም አማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን ያሉ የምርጫ ስራ የቆመባቸው ቦታዎችን ጨምሮ እንደየሁኔታው በነዚህ ከላይ በተጠቀሱት ቦታዎች የመራጮች ምዝገባ የሚጀመርበትን ሁኔታ እና ቀናት ቦርዱ የሚያሳውቅ ይሆናል።
4. 1500 ሰዎቸን መዝግበው በጨረሱ ምርጫ ጣቢያዎች ተጨማሪ ንኡስ ምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት የሚቀጥል ይሆናል።
በዚህም መሰረት ፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎች ፣ ሲቪል ማህበራት የመራጮች ምዝገባን ለማበረታታ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉ ምርጫ አስፈጻሚዎችም በዚሁ መሰረት የመራጮች ምዝገባን እንዲያከናውኑ እያሳሰበ ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች የመራጮች ካርድ እነዲወስዱ ያበረታታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.