Fana: At a Speed of Life!

የመስቀል በዓል ኮቪድ-19 ለመከላከል ሲባል የተወሰነ ምዕመናን በተገኙበት ይከበራል – የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10 ፣ 2013(ኤፍ.ቢ.ሲ) የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል የኮቪድ-19 ወረርሽ መከላከልን መሰረት አድርጎ የተወሰኑ ምዕመናን በተገኙበት እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስታወቀች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፓትርያርኩ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ÷መስቀል ቤተክርስቲያኗ ከምተከብራቸው የአደባባይ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

የመስቀል ደመራ በየዓመቱ በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ስርአት ብዙ ህዝብ ተገኝቶ የሚያከብረው በዓል መሆኑንም አስታውሰዋል።

የዘንድሮው የደመራ በዓል ግን ስርዓቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ አነስተኛ ምዕመናን በተገኙበት እንደሚከበር ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ገልጸዋል።

በዚህም በአጠቃላይ እስከ 5 ሺህ ተሳታፊዎች በመስቀል አደባባይ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተናገሩት።

ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ አያይዘውም በዘንድሮ በዓል የተሳታፊ ሰዎች ቁጥር የተወሰነው ካለው ወቅታዊ የወረርሽኙ ሁኔታና መስቀል አደባባይ በአሁኑ ወቅት ማስተናገድ የሚችለውን መጠን ግምት ውስጥ በማስገባት ሲሆን ይህንንም የጠቅላይ ቤተክህነት ለሚመለከተው አካል አሳውቋል ነው ያሉት።

የመስቀል አደባባይ ለበዓሉ ዕለት ክፍት እንደሚሆንና ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መግለጹንና ይሄንንም በአካል ተገኝቶ መመልከቱን አስረድተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.