Fana: At a Speed of Life!

የመስቀል ደመራ በዓልን በተለመደው ብዛት ተሰባስቦ ማክበር የኮሮና ቫይረስ ተገላጭነትን ስለሚያሳድግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል-የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመስቀል በአልን በተለመደው ብዛት ተሰባስቦ ማክበር የኮሮና ቫይረስ ተገላጭነትን ስለሚያሳድግ ከፍተኛ ጥንቃቄ አንዲደረግ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድና ስርአት በዓሉ በበርከታ የሀገር ውስጥ እና ለበአሉ ሲሉ ከተለያዩ ሀገራት በሚሰባሰቡ ሰዎች ደምቆ ይከበር የነበረ ቢሆንም፤ ዘንድሮ ግን ወቅታዊው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በነባሩ ድምቀት በዓሉን ለማክበር አልፈቀደም።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ እንደሚሉት፤ በሀገር አቀፍ ደረጀ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እየጨመረ በመምጣቱ የበዓሉን ታዳሚዎች መጠን መቀነስ አስፈልጓል።
በዓሉ በዚህ መልኩ ቢከበር ይሻላል የሚለው ሀሳብም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስተያን ጋር ውይይት ተደርጎበት ከውሳኔ ላይ ተደርሷል ብለዋል።
በመሰል በዓላት ወቅት ህብረተሰቡ ወደ ተለያዩ አከባቢዎች አንደሚንቀሳቀስ ያነሱት ሚኒስትር ፌኤታዋ፤ ህብረተሰቡ እንደ አለምም እንደ ሀገርም ያለንበትን የወረርሽን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንቅስቅሴዎችን መገደብ እንዳለበት ገልፀዋል።
አስገዳጅ የሆኑ ሁኔታዎች ሲኖሩ ደግሞ አስፈላጊውን የጥንቃቄ መንገድ መተግበር ይገባል ብለዋል።
የመስቀል በዓል በተለየ ትኩረት እና ድምቀት ከሚከበርባቸው ክልልች መካከል የአማራ እና ደቡብ ክልል ይጠቀሳሉ።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ታሪኩ በላቸው በክልሉ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያደገ በመምጣቱ በዓሉን በቀደመ ልማድ በስፋት ተሰባስቦ ማክበር ለበለጠ አደጋ ያጋልጣል ነው ያሉት።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህን እንዲገነዘብ በመገነኛ ብዙሃን ከሚተላለፉ መልእክቶች ባሻገር በእምነት ተቋማት፣ በባለሞያዎች እና በአመራሮች አማካኝነት የማስተማር ስር እየሰራ ነው ብለዋል።
የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ አጥናው ካውዛም በክልሉ በየእለቱ በቫይርሱ የሚያዙ ሰዎች መጠን እየጨመረ መሆኑን የሚያሳይ ቢሆንም ፤ የህብረተሰቡ የመጠንቀቅ ልምድ ግን መጨመር ሲገባው ቀንሷል ነው ያሉት።
በደቡብ ክልል የመስቀል ደመራ በዓልን ለማክበር ወደ ቤተሰብ የመጓዝ ሰፊ ልማድ አንደመኖሩ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ይህ ልምድ አንዲቀየር ክልሉ ሰፊ የማስተማር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የጤና ቢሮ ሀላፊዎቹ እንዳሉት ነባሩን ልምድ እና ባህል መተው ቀላል ባይሆንም አደጋውን ግምት ውስጥ በማስገባት ህብረተሰቡ እራሱን ከሚየሳጣው አላስፈላጊ ድርጊት በመቆጠብ በዓሉን አንዲያከብር ጠይቀዋል።
በትእግስት አብርሀም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.