Fana: At a Speed of Life!

የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ ከነገ ጀምሮ የቁጥጥር ዘመቻ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ ከነገ ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የቁጥጥር ዘመቻ በአዲስ አበባና በአራት ክልሎች እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የመንገድ ደህንነት እና የመድህን ፈንድ አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን በተሰሩ ከጳጉሜ እስከ ጳጉሜ እና መንገድ ለሰው የህዝብ ንቅናቄዎች ከ34 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ገልጿል።

እስካሁን በተሰራው ስራም በ2010 ዓ.ም በ10 ሺህ ተሽከርካሪ 55 ሰው ይሞት የነበረ ሲሆን ÷ይህን ቁጥር በ2013 ዓ.ም ወደ 32 ነጥብ 6 መቀነስ መቻሉን አስረድተው በዚህ ዓመትም ወደ 30 ለመቀነስ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአገልግሎት መስጫው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አባሱ÷ በተሰራው ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ መልካም ውጤት መገኘቱን ገልጸው ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የሞት መጠን በተወሰነ ደረጃ መቀነሱንና የንብረት ውድመት ግን ቁጥሩ እንደጨመረ ገልጸዋል።

በወቅቱ በተለይ የቁጥጥር ስራ የሚሰሩት የጸጥታ አካላት ትኩረታቸው ወደ ህልውናው ዘመቻ ስለነበር የቁጥጥር ስርዓቱ ላልቶ እንደነበርም አስታውሰው አሁንም ለመንገድ ደህንነት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከነገ ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የቁጥጥር ዘመቻ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

በቁጥጥር ዘመቻው በፌደራል የቁጥጥር አካላት በአዲስ አበባ ፣በኦሮሚያ ፣በአማራ፣ በደቡብ እና በሲዳማ ክልሎች ቁጥጥር ለማድረግ 150 ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች መለየታቸውን የገለፁ ሲሆን ÷ከዚህ በተጨማሪ ክልሎችም በራሳቸው መንገድ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ይደረጋል ብለዋል።

በፌደራል ፖሊስ የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ ሃላፊ የሆኑት ኮማንደር ደነቀ ክፍሌ ÷ሁሉም አካላት ይህ አሰራር ውጤታማ እንዲሆን በመናበብ እንዲሰሩና እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.