Fana: At a Speed of Life!

የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓትን ለማሻሻል የገንዘብ ሚኒስቴር አዲስ ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ለማሻሻል የመንግስትን የበጀት ፣ የፋይናንስ እና የሂሳብ አያያዝ ስራዎችን የሚደግፍ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓት ፕሮግራም ተደራሽነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታውቋል።
ይህ የተገለጸው አዲሱ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓት ስትራቴጂክ እቅድ ለዋና ዋና ባለድርሻ አካላት በቀረበበት ወቅት ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጋ መንግስቱ፥ በሁለተኛው የስትራቴጂክ ዘመን ሊደረስባቸው የታለሙ ቁልፍ ውጤቶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የፕሮግራሙን ውጤታማነት ለማሳደግ፣ የተሻሻሉ መሠረተ ልማቶች በመጠቀምና ተቋማዊ አሠራሮችን የበለጠ በማሳደግ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ተጨማሪ 760 ጣቢያዎችን ለመድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ስትራቴጂክ ዕቅዱ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየተከናወኑ ከሚገኙ የተለያዩ የፋይናንስ አስተዳደር ማሻሻያዎች ጋር የተያያዘ እና ለኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ ለበጀት አመዳደብ፣ የገቢ አሰባሰብ እና የወጪ አያያዝን ለማዘመን የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግስተ ፋይናንስ ስርዓትን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተብራርቷል።
አቶ ነጋ በመጀመሪያው የስትራቴጂክ ዘመን በአውሮፓውያኑ 2016-2020 በፕሮግራሙ ወደ 156 ጣቢያዎች እንደተዘረጋ፣ ስለፕሮግራሙ ለ14 ሺህ 773 የመጨረሻ ተጠቃሚዎች ስልጠና መሰጠቱን፣ የፕሮግራሙን ትግበራ ለመደገፍ የሚያስችል በቂ የውስጥ አቅም መገንባቱን አብራርተዋል።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ከፌዴራል መንግሥት በጀት ውስጥ 84 በመቶ የሚሆነው በተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓት እየተዳደረ ነው ብለዋል።
የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓት በመጀመሪያው ስትራቴጂካዊ ወቅትም ከ25 ሚሊየን በላይ ግብይቶችን አስተናግዷል።
ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓትን ከሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ እና ገቢ ጋር ከመሳሰሉ የመረጃ ስርዓቶች፣ ከብድር አስተዳደር፣ የፋይናንስ መረጃ ትንተና፣ ከብሄራዊ ባንክ፣ ከንግድ ባንክ እንዲሁም ከገቢዎች ጋር የማዋሃዱን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓት ስኬታማ ትግበራ ወቅታዊ ፣ ተገቢ እና አስተማማኝ የፋይናስ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግነት የሚያስችል መሆኑንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.