Fana: At a Speed of Life!

የመከላከያ አካዳሚክ ዲን የነበሩት ብ/ጄ አሊጋዝ ገብሬን ጨምሮ አራት የጦር መኮንኖች ለ4ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የመከላከያ አካዳሚክ ዲን የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል አሊጋዝ ገብሬን ጨምሮ አራት የጦር መኮንኖች ለ4ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 2ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች 1ኛ ብርጋዴር ጄኔራል አሊጋዝ ገብሬ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረስላሴ በላይ፣ ብርጋዴር ጄኔራል አብርሃ ታደሰና ሻምበል ወልዳይ ሰመረ ናቸው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ አባላት በተጠረጠሩበት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ ወንጀል ከዚህ በፊት ፍርድ ቤቱ በሰጣቸው 11 ቀናት የምርመራ ጊዜ የሰሩትን ምርመራ አቅርበዋል።

በዚህም የጦር መኮንኖቹ ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን የሰሜን እዝ እንዲመታ ማድረጋቸውን እና ለኦነግ ሸኔ ቡድን በስውር ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር በማስረጃ አረጋግጫለሁ ብሏል መርማሪ ፖሊስ፡፡

በተጨማሪም የትግራይ ክልል ተወላጆችን ለትግራይ ልዩ ሃይል በመመልመል ልዩ ሃይሉን እንዲቀላቀሉ ሲያደርጉ እንደነበርም መረጃ መሰብሰቡን ጠቅሷል።

በዚህ ልክ የተሰሩ በርካታ የምርመራ ስራዎችን የገለጹት መርማሪዎቹ ለቀሪ ማለትም፤ በትግራይ በተለያዩ ጊዜያት ተገለው በጅምላ የተቀበሩትን ጨምሮ በግፍ የተገደሉ ንጹሃንን አስከሬን ምርመራ ውጤት ለማምጣት የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በየሆስፒታሉ ህክምና ላይ ያሉትን የህክምና ውጤት ለማምጣት እና የወደመውን የህዝብ ሃብት መጠን ለይቶ ለማቅረብ ከወንጀሉ ስፋት አንጻር የተጀመሩ ምርመራዎችን ለማጠናከር ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው የወንጀል ተሳትፏችን ተለይቶ አልቀረበም፤ በዚህ ልክም ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም፤ በዋስ ወጥተን ጉዳያችን በውጭ እንከታተል ሲሉ የዋስትና ጥያቄ አንስተዋል።

ጉዳዩን የተከታተለው ችሎቱም መዝገቡን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለታሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ከዚህ በፊት የተጠርጣሪዎቹ የታገደ ደመወዝና ንብረትን በተመለከተ እግዱ ይነሳልን ባሉት አቤቱታ ላይ ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቢሮ ከሚመለከተው ዘርፍ ቀርቦ አስተያየት እንዲሰጥ ትዕዛዝ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ቀርቦ አስተያየት የሰጠ አካል አልተገኘም።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.