Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 83ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ የጂኦተርማል ሀብት ልማት ዐዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ ዐዋጅ ላይ የተወያየ ሲሆን፥ የዐዋጁን የተወሰኑ ድንጋጌዎች ለማሻሻል የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባቀረበው የማሻሻያ ዐዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል።

ከዚህ ባለፈም የጤና ሚኒስቴር የኮቪድ19 ወረርሽኝን በመከላከልና የሕክምና አገልግሎት በመስጠት በቀጥታ ለሚሳተፉ የጤና ዘርፍ ሠራተኞች የማበረታቻ አበል ክፍያን ለመወሰን ባዘጋጀው መመሪያ ላይ ከተወያየ በኋላ በሥራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።

በተጨማሪም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በኢኮኖሚው ላይ የተከሰተውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እና የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ለመሸፈን የ2012 በጀት ዓመት የተጨማሪ በጀት ረቂቅ ዐዋጅ እንዲሁም የመካከለኛ ዘመን (የ2013-2017) የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ በመወያየትም አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ዐዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ እንዲሁም ማዕቀፉም በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

እንዲሁም በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በተዘጋጀውና ለሕዝብ ጥቅም መሬት ሲለቀቅ ስለሚከፈል ካሳ እና የልማት ተነሺዎችን መልሶ ስለማቋቋም በወጣ ደንብ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና በሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑን ምክር ቤቱ ለጣቢያችን በላከው መግለጫ አስታውቋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.