Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ም/ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 93ኛው መደበኛ ስብሰባ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 93ናው መደበኛ ስብሰባ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በካፒታል ገበያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን ያደገና የዳበረ የካፒታል ገበያ ለሃገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል፡፡
የካፒታል ገበያ ባደገበት ሃገር አምራች ኩባንያዎች የአክስዮንና የብድር ሠነዶችን በመሸጥ የረዥም ጊዜ እና የአደጋ ሥጋት ያለባቸውን ነገር ግንየምርታማነት ባህሪ ያላቸው ፕሮጀክቶች በቀላሉ ፋይናንስ ማድረግ ይችላሉም ነው ያለው፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ የካፒታል ገበያ ለህብረተሰቡ አማራጭ የቁጠባ መንገዶችን በማቅረብ የኢኮኖሚውን የፋይናንስ ቁጠባ ከፍ ያደርገዋል፡፡
ይህም ኢንቨስትመንትን በሃገር ውስጥ ቁጠባ ፋይናንስ እንዲሆን በማድረግ ከውጭ ፋይናንስ ያለንን ጥገኝነት ይቀንሰዋል ብሏል፡፡
በዚህ ረገድ የካፒታል ገበያ የሃገሪቱን የክፍያ ሚዛን በማስተካከል ለማክሮኢኮኖሚ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡
እነዚህንና ሌሎች የካፒታል ገበያ ጥቅሞችን ታሳቢ በማድረግ ረቂቅ አዋጁ በብሄራዊ ባንክ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን÷ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲመራ ወስኗል፡፡
በመቀጠልም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ለማቋቋምና ለማስተዳደር በወጣ
ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት በተለይም የባንኮችና የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ሀብትበአብዛኛው የአስቀማጮች መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በመሆኑም የገንዘብ አስቀማጩን ጥቅም ለመጠበቅ መንግሥታትበፋይናንስ ተቋማቱ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል፡፡
ጠንካራ የፋይናንስ ቁመና ያለዉ “ግልፅ”የተቀማጭ ገንዘብ መድን ሥርዓት በተፋጠነ ሁኔታ ብዛት ላላቸዉ አስቀማጮች ገንዘባቸዉን በመመለስ በፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ ያለዉ የሕዝብ አመኔታ እንዲጨምር ያደርጋል ተብሏል፡፡
ይህም በተቀማጭ መልክ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ፋይናንስ ዘርፍ እንዲገባ በማድረግ ለኢንቨስትመንትና ለፋይናንስ ሥርዓቱ ጥልቀት ስፋትና አካታችነት እንዲሁም ለኢኮኖሚዉ ዕድገት የበኩሉን አስተዋፅዖ የሚያደርግ መሆኑን በመግለጽ ብሄራዊ ባንክ ረቂቅ ደንቡን አዘጋጅቶ ማቅረቡ ተገልጿል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገበኋላ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ቁጥር 100/201 ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የመከላከያ ሰራዊት አደረጃጀት እና አሰራር ዘመኑን በዋጀ እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ግምት ውስጥ አስገብቶ በየጊዜው እየተፈተሸ ሊስተካከልና ለውጥ ሊደረግበት የሚገባ ዘርፍ ነው ተብሏል፡፡
ሰራዊቱ እናት አገሩንአሁን ካለው የበለጠ ዘመን ሊያገለግል የሚችልበትን እድል መፍጠር እና አገሪቷም ወጪ አውጥታ፣ ጊዜ ወስዳ ያሰለጠነቻቸውን እና ለአገራዊ ተልዕኮ እና ግዳጅ ብቁ አድርጋ ለተልዕኮ ያሰማራቻቸውን የሰራዊት አባላት ብቁ እና ዘመኑን የሚመጥን አገልግሎት እስከሰጡ ድረስ በሰራዊቱ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውንየአገልግሎት ዘመን እንደገና መፈተሽና ማስተካከል አስፈላጊ በመሆኑ የአገርን ሉዓላዊነት በማስከበር፣ህገመንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ በመጠበቅ፣የህዝቦችን ዘላቂ ሰላም እና አብሮ የመኖርዋስትና በማረጋገጥ ረገድ ዋጋ የከፈሉ እና እየከፈሉ የሚገኙ የሰራዊት አባላትን ለአገር የከፈሉትን ውለታ ሊተካ የሚችል ባይሆንም የአገሪቱ አቅም በፈቀደው መጠን ሊያገኟቸው የሚገቡ አገልግሎቶችን፣ሊደረግላቸው ስለሚገባ ማበረታቻ እና አለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን እና አሰራሮችን እንዲሁም የሰራዊቱንነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የሰራዊቱ አባላት እና ኃላፊዎች ልዩ የማዕረግ እድገት እና ሽልማት ሊያገኙ የሚችሉበትን አዳዲስ አሰራሮች በአዋጁ ውስጥ ማካተት በማስፈለጉ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁን ተዘጋጅቶ መቅረቡ ተገልጿል።
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲመራ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.