Fana: At a Speed of Life!

የማህበረሰብ ንቅናቄ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የመከላከሉ ስራ ማዕከል መሆን ይገባዋል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የማህበረሰብ ንቅናቄ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የመከላከሉ ስራ ማዕከል መሆን እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

ብሔራዊ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ተከላካይ ምክር ቤት ዛሬ መደበኛ ስብሰባውን አድርጓል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ችግሩን ስር ነቀል በሆነ መንገድ ለመቅረፍ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ገንዘብን መሰረት ባደረጉ ጥቂት ደላሎች ምክንያት የደሃ ልጆች እየተጎዳ የሚቀጥልበት ሂደት መቆም አለበትም ብለዋል።

ወንጀሉን የመከላከሉ ስራ ማዕከልም የማህበረሰብ ንቅናቄ መሆን እንደሚገባው ጠቅሰው፥ ከዚህ አንጻር ቤተሰብ ትልቁን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።

የግንዛቤና የአዕምሮ ልማት ማዕከል የሆኑ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አላስፈላጊ ከሆኑ ሁከቶች ወጥተው ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ማፍራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ግልጽነት የጎደለውና ከሌሎች ህጎች ጋር የማይጣጣም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ማሻሻል በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመራቱ ተገልጿል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በበኩላቸው ወንጀሉ በምስጢር የሚሰራና በርካታ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑ የመከላከልና ህግ የማስከበሩን ስራ አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቅሰዋል።

ተሳታፊዎች የቅንጅት ጉድለት እና የስራ እድል ፈጠራ ወንጀሉን የመከላከሉን ስራ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሳካ አድርጓል ማለታቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.