Fana: At a Speed of Life!

የምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች በዲሞክራቲክ ኮንጎ ወታደራዊ ኃይል ለማሰማራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግርን ለመዋጋት የምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች በዲሞክራቲክ ኮንጎ ወታደራዊ ኃይል ለማሰማራት መስማማታቸው ተገልጿል፡፡

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል የታጠቁ ኃይሎችን የሚመክት ቀጣናዊ ኃይል ለማቋቋም በቀጠናው መሪዎች የተደረገውን ስምምነት መቀበሏን አስታውቃለች፡፡

በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው የቀጠናው መሪዎች ጉባኤ ላይ የዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ብሩንዲ፣ ዑጋንዳ እና የሩዋንዳ መሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፥ ከቀጠናው የተወጣጣ እና በዲሞክራቲክ ኮንጎ የሚሰማራው ወታደራዊ ጦር በአስቸኳይ እንዲቋቋም መመሪያ ሰጥተዋል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአፍሪካ ትልቁ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ኃይል የሚገኝባት ሀገር ብትሆንም የሀገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል አሁንም መረጋጋት አይታይበትም ተብሏል፡፡

አላይድ ዲሞክራቲክ ፎርስ (ADF) ተብሎ የሚጠራው እና ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ የሚጠረጠረው ታጣቂ ቡድን፥ የማዕድን ሀብት በሚገኘበት ዲሞክራቲክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል በመዘዋወር ጥቃቶችን እንደሚፈፅም ተመላክቷል፡፡

የሩዋንዳ ነፃ አውጪ ተብሎ የሚጠራው የሚሊሻ ኃይል ሌላኛው የቀጠናው ስጋት የሆነ ቡድን መሆኑም የተገለፀ ሲሆን፥ ቡድኑ በ1994 በሩዋንዳ ቱትሲዎች ላይ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተሳትፎ በነበራቸው ሰዎች የሚመራ ነውም ተብሏል፡፡

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኙ የውጭ ሀገር ታጣቂ ቡድኖች በፍጥነት ቀጠናውን ለቀው ወደየአካባቢያቸው እንዲሄዱም በምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች መመሪያ የተሰጠ ሲሆን፥ በሀገሪቱ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖችም ወታደራዊ መፍትሄን ከመፈልግ ይልቅ በፍጥነት ወደ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲገቡ መሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡

በቀጣይም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፊሊክስ ቲሺኪዲ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአካባቢ ታጣቂ ቡድን ተወካዮች መካከል ውይይት እንደሚጀመርም በመሪዎቹ ስብሰባ ተነስቷል፡፡

መሪዎቹ በየወሩ በመገናኘት የተደረጉ ለውጦችን ለመገምገም መወሰናቸውንም ሲ ጅቲኤን አፍሪካ በዘገባው አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.