Fana: At a Speed of Life!

የምሥራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ተጀመረ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ አዘጋጅነት የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል።

በዚሁ ወቅት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት  እንደገለጹት÷ እንደዚህ አይነት ውድድሮች የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጎልበትና ስፖርትን ለማሳደግ  ያግዛሉ፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጃገዊ ሮበርት በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት ያደረገችውን ዝግጅት  አድንቀው÷ ኢትዮጵያ ለውድድሩ ተሳታፊዎች፣ ስፖርተኞችና የልዑካን ቡድኑ አባላት ላደረገችው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ውድድሩ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት መካሄዱ በቀጣይ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ልምድ የሚገኝበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ብዛኔ ናቸው፡፡

የውድድሩ ተሳታፊ አገራት በወንዶችና ሴቶች ምድብ በእያንዳንዳቸው አምስት አትሌቶችን የሚያሳትፉ ሲሆን÷ ኢትዮጵያ የውድድሩ አዘጋጅ በመሆኗ ተጨማሪ አትሌቶችን የማሳተፍ አድል አግኝታለች፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ 10 ወንድና 10 ሴት አትሌቶችን በውድድሩ የምታሳትፍ ይሆናል፡፡

በዚህ ውድድር አሸናፊ የሆኑ አትሌቶች በ2022 አልጀሪያ በምታዘጋጀው የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና የሚካፈሉ ይሆናል፡፡

እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2014 በሚቆየው የምሥራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኮሞሮስ፣ ሩዋንዳ፣ ሲሸልስ፣ ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ ኡጋንዳ እና ሞሪሺየስ ይሳተፋሉ ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.