Fana: At a Speed of Life!

የምርጫ ጉዳዮች በፍርድ ቤት የሚስተናገዱበት የስነ ስርዓት እና የማስረጃ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የምርጫ ጉዳዮች በፍርድ ቤት የሚስተናገዱበት የስነ ስርዓት እና የማስረጃ ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱ ተገለጸ።

በረቂቅ ደንቡ ላይ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶች፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንቶች እና ዳኞች በተገኙበት ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

ቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማስቻል የደንቡ መዘጋጀት ወሳኝ መሆኑም ተገልጿል።

ማንኛውም በመራጭነት ከመመዝገብ ያለአግባብ ተከልክክያለሁ አልያም መመዝገብ የሌለበት ግለሰብ ተመዝግቧል ያለ አካል ለምርጫ ክልሉ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አቤቱታ አቅርቦ በ5 ቀናት ውሳኔ ካልተሰጠው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዞ መቅረብ እንደሚችል በረቂቅ ደንቡ ላይ ሰፍሯል።

ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘም ፍርድ ቤቱ በ10 ቀናት ተከራካሪዎችን መርምሮ በ4 ቀናት ውስጥ ውሳኔ እንደሚሰጥ ተቀምጧል።

ከእጩዎች ምዝገባ ጋር በተገናኘም ፍርድ ቤቱ በ15 ቀናት ተከራካሪዎችን መርምሮ በ4 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል።

የምርጫ ጉዳዮች በፍርድ ቤት በሚስተናገዱበት የስነ ስርዓት እና የማስረጃ ረቂቅ ደንብ ውስጥ ከምርጫ ምልክት፣ ከስነ ምግባር ጥሰቶች እና ድምጽ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ የሚነሱ አቤቱታዎችን ለመዳኘት የሚያስችሉ ዝርዝር ነጥቦች ተካተውበታል።

ከድምጽ ቆጠራ ሂደትና ውጤትን የተመለከቱ አቤቱታዎችን በተመለከተም ጉዳዩ ለፍርድ ቤቱ ቀርቦ በ3 ሰዓታት ውስጥ ይመረመራል ተብሏል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ በምርጫ አዋጁ አንቀጽ 155(6) መሰረት አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን ቅሬታ የቀረበበት የምርጫ ክልል ውጤት እንዳይገለጽ ሊያዝ እንደሚችል በረቂቅ ደንቡ ሰፍሯል።

ፍርድ ቤቱ አቤቱታው በቀረበለት በ30 ቀናት ውስጥም ውሳኔ ይሰጣልም ነው የተባለው።

በረቂቅ ደንቡ ላይ በፍርድ ቤት ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ በድጋሜ ዳኝነት እንዲታይ ጥያቄ ሊቀርብ እንደማይችልም ተቀምጧል።

በምስክር ስናፍቅ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.