Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ሀይል በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንዲሰማራ ፕሬዚዳንት ኬንያታ ጠየቁ 

አዲስ አበባ፣ሰኔ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ሀይል በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንዲሰማራ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጠይቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል ያለበትን የፀጥታ ችግር ወደ ነበረበት ለመመለስ በማሰብ ነው የቀጠናው ተጠባባቂ ሀይል እንዲሰማራ የጠየቁት፡፡

ለሳምንታት በቆየው ሁከትና ብጥብጥ ዴሞከራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ዲፐሎማሲያዊ ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸውን ያመላከቱት ፕሬዚዳንቱ ኤም 23 የተባለውን የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አማፂ ቡድን ለሁከቱ ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

ቀጠናዊ ሀይሉ ቢሰማራ የሁለቱን ሀገራት የጸጥታ ችግር እንደሚፈታና እየተባባሰ የመጣውን የዲፕሎማሲ ውጥረት ለማብረድ እንደሚረዳም አስታውቀዋል።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሩዋንዳ ለአማፂያኑ ድጋፍ እየሰጠች ነው በሚል ሩዋንዳን መወንጀሏን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት እርስ በእርስ ግጭት ውስጥ መግባታቸው ተዘግቧል፡፡

በሃገሪቱ የሚንቀሳቀሱ አማፂያን ከሩብ ምዕተ ዓመት በፊት በነበረው የሀገሪቱ እርስ በርስ ጦርነት የተፈጠሩ መሆናቸውን ሲ ጀ ቲ ኤን አፍሪካ እና ባሮን ኒውስ ዘግበዋል፡፡

የምሰራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ሀይል የኡጋንዳ፣ የብሩንዲ፣ የሩዋንዳ እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሪዎች በሚያዚያ ወር በናይሮቢ ባደረጉት ስብሰባ ላይ እንዲቋቋም መወሰናቸው የሚታወስ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.