Fana: At a Speed of Life!

የምታጋሩት ባይኖር እንኳን ፍቅራችሁን አጋሩ – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መስጠት አንደማያጎድል በመገንዘብ አጠገባችሁ ለሚኖሩ ሰዎች ማዕድ አጋሩ፤ የምታጋሩት ባይኖር እንኳን ፍቅራችሁን አጋሩ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዛሬው ዕለት ከ195 ሺህ በላይ ለሆኑ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር አከናውኗል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በከተማ አስተዳደር ደረጃ የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብርን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት፥ “ከሕዝባችን ጋር አብረን እንዳለን፣ ስለእነሱ እንደምናስብ፣ እንደምንጨነቅ እና ካለን በማካፈል እነሱን እንደምናገለግል የምንገልፅበት ፕሮግራም ነው” ብለዋል፡፡
አክለውም መስጠት አንደማያጎድል በመገንዘብ አጠገባችሁ ለሚኖሩ ሰዎች ማዕድ አጋሩ፤ የምታጋሩት ባይኖር እንኳን ፍቅራችሁን አጋሩ ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የማዕድ ማጋራት ዓላማው አሁን ያለውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ማቃለልና መደጋገፍ በመሆኑ÷ በከተማችን ደጋፊ እና ጠያቂ የሌላቸው በርካታ ሰዎች አሉ ለእነዚህ ወገኖች ድጋፍ ልናደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አስተዳደሩ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ ምርትን በማሳደግ ተግቶ በመስራት፣ ስንፍናን በማስወገድ፣ የአኗኗር ዘይቤን በማሻሻል፣ የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር እና በከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ማለታቸውን ከከንቲባ ጽሕት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ህብረተሰቡም በዚህ ስራ ላይ ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበው፥ ለዚህ ተግባር አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች ለንግዱ ማህበረሰብ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በዚህ ወቅት ለህዝቡ ማዘን አለባችሁ፤ ለትርፍ ብቻ ሳይሆን ዜጎችም እንዳይጎዱ ለህሊናችሁ ልትሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.