Fana: At a Speed of Life!

የምዕራባዉያኑን ዲፕሎማሲያዊ ጫና አሸንፎ ለመዉጣት ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መስራት ይገባል – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የምዕራባዉያኑን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመቋቋምና አሸንፎ ለመዉጣት ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የህግና ታሪክ መምህር ዶክተር አልማዉ ክፍሌ÷የአፍሪካዉያን ወደ ትብብር መምጣት አሜሪካንን ጨምሮ ለምዕራባዉያኑን ምቾት የሚሰጥ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድና በአህጉሩ የኢትዮጵያ ተጽእኖ ፈጣሪነት ማደግ ምዕራባዉያኑን እንደሚያሳስባቸዉ ያብራሩት ዶክተር አልማዉ÷ ምዕራባዉያን የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካን በበላይነት ለመዘወር ያላቸዉ ፍላጎት ኢትዮጵያን የትኩረት ነጥብ አድርጓታል ብለዉም እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ፍሬዉ ይርጋለም÷ ምዕራባዉያኑ በኢትዮጵያ እንዲፈጠር የሚፈልጉት ደካማ መንግስት አለመመስረት ሃገሪቱ ላይ ጫና እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

አሜሪካ እና ምዕራባዉያኑ በቀይ ባህር ቀጠና የምስራቁ ምጣኔ ሃብት ላይ ጫና ለማሳደር ያላቸዉ እቅድና አለም አቀፍ ገበያዉን በበላይነት የመቆጣጠር ግብ አሁንም እንደቀጠለ ምሁራኑ አስረድተዋል።

ተገዳዳሪያቸዉ ቻይና ከአፍሪካ ሃገራት ጋር እየመሰረተች የምትገኘዉ ባለ ብዙ ወገን ግንኙነት ምዕራባዉያኑ ለቀጠናዉ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓልም ብለዋል ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራኑ።

ኢትዮጵያ ላይ አሁን የበረታዉን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመቀልበስ ብሎም አሸንፎ ለመዉጣትም እንደ ሃገር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መቅረፍ ቅድሚያ ሊሰጠዉ ይገባልም ብለዋል ።

አንድነትን ማጠናከር፣ ከምዕራባዉያኑ ጥገኛ የሆንባቸዉ ሸቀጦች በሃገር ዉስጥ እንዲመረቱ ብርቱ ስራዎችን ገቢራዊ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል ምሁራኖች፡፡

በተመሳሳይ የምራባዉያኑን ጫና ተቋቁመዉ አሸናፊ ከሆኑ ቱርክ እና ኢራንን ከመሰሉ ሃገራት ትምህርት መዉሰድና ከጎረቤት እንዲሁም ከሌሎች ሃገራት ጋር ጠንካራ የንግድና ምጣኔ ሃብት ግንኙነት ማድረግ እንደሚገባም ምሁራኑ መክረዋል ።

በአወል አበራ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.