Fana: At a Speed of Life!

የምዕራብ ጎንደር ባለሀብቶች ለሕልውና ዘመቻው ስኬት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋገጡ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሽብርተኛው ህወሓት ከተጋረጠው ወቅታዊ የሕልውና አደጋ ኢትዮጵያን ለመታደግ ለሚደረገው ሁሉን አቀፍ ትግል ስኬት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የምዕራብ ጎንደር ዞን ባለሀብቶች አስታወቁ።

በዞኑ በእርሻ ኢንቨስትመንትና በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶችና ነጋዴዎች ለሕልውና ዘመቻው ከ21 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

አቶ መሳፍንት ገበየሁ በዞኑ ምዕራብ አርማጭሆ “ኮረደም የእርሻ ጣቢያ” በግብርና ልማት የተሰማራው አሊያንስ ስታር ግሩፕ ሥራ አስኪያጅ ናቸው።

አቶ መሳፍንት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ፥ የአሸባሪው ህወሓትን ሀገር የማፍረስ ተልኮ ለማምከን እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ትግል ስኬት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለዚህም ቀደም ሲል ከ2 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውስው ÷ ጠላትን ሲፋለሙ ጉዳት ለደረሰባቸው የፀጥታ አባላትም 65 በጎችን በድጋፍ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

“ሰርቶ መለወጥና መጠቀም የሚቻለው ሀገር ሲኖር ነው” ያሉት ሥራ አስኪያጁ ÷ ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ህወሓት ጥፋት ለመታደግና የህዝቡን ህልውና ለማስጠበቅ ድርጅቱ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ብለዋል።

ሌላኛው በመተማ ወረዳ “ደለሎ የእርሻ ልማት ጣቢያ” በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ጌትየ ገብሩ እንዳሉት ÷ “ለህልውና ዘመቻው ሁሉም ድጋፍ በማድረግ የኢትዮጵያን ጠላት ማንበርከክ ይገባል”።

ቀደም ሲል 300 ሺህ ብር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ጌትየ ፥ በቀጣይም ከሌሎች ባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት የሚጠበቅባቸው ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

“አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ ለሚደረግ የህልውና ዘመቻ የሚቆጠብ ሃብት አይኖረኝም” ያሉት ደግሞ በገንዳ ውሃ ከተማ በንግድ ሥራ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ አዲሱ ብሩክ ናቸው።

በለሀብቱ እንዳሉት ቀደም ሲል 450 ሺህ ብር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ÷ ድጋፋቸውን ወደፊትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያረጋገጡት።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው፥ በዞኑ የሚገኙ ባለሃብቶች ለህልውና ዘመቻው እያደረጉ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ የሚገኙ ባለሃብቶችና ነጋዴዎች እስካሁን ለሕልውና ዘመቻው ስኬት 21 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውንም ነው የተናገሩት።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.