Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያና – ዩክሬን ጦርነት የዓለምን የምግብ አቅርቦት ዕጥረት እንደሚያባብሰው ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት የዓለምን የምግብ አቅርቦት ዕጥረትን እንደሚያባብሰው “ኬር” የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት ያላሄደው ዓለም አቀፍ የዳሰሳ ጥናቱ አመላከተ፡፡

አፍሪካ በገቢ ንግድ አብዛኛውን የስንዴ እና የምግብ ዘይት አቅርቦቷን ከሩሲያ ታገኛለች፡፡

በመሆኑም ተባብሶ የቀጠለው የሩሲያና – ዩክሬን ግጭት እልባት ካላገኘ ወደ አፍሪካ ሀገራት ይገባ የነበረው አቅርቦትን በማስተጓጎል በአህጉሪቱ ሀገራት ችግር ላይ እንደሚወድቁ ነው የተመለከተው፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በድኅነት አረንቋ ውስጥ ሆነው በምግብ እጥረት ውስጥ የሚኖሩ 811 ሚሊየን ሰዎች ይገኛሉም ነው የተባለው፡፡

“ኬር” ÷ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት በአፋጣኝ ማሰራጨት ካልተቻለም ሚሊየኖች በተለይም ሴቶችና ሕጻናት ሊጎዱ እንደሚችሉ ነው ያመላከተው፡፡

እንደ ጥናቱ ከሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት በፊት ጀምሮ እየተከሰቱ ላሉት የምግብ እጥረት ቀውሶች መነሻቸው የዓለም የዓየር ንብረት ለውጥ እና በሀገራት ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶች ናቸው፡፡

በየጊዜው እየተባባሳ ያለውን የዓለም የዓየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳረፉንና ሰዎችም ቀያቸው ትተው እንዲፈናቀሉ የበኩሉን ሚና እንደተጫወተ ጥናቱ አመልክቷል፡፡

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እና በመካከለኛው አሜሪካ ደረቃማ አካባቢዎች ያሉ ዜጎች በዓየር ንብረት ለውጡ ሳቢያ በአካባቢያቸው ለገበያ የሚቀርብ አጥጋቢ ምርት እንዳያገኙ ማድረጉም ተመልክቷል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ መውደቅ ከኮቪድ 19 ሥርጭት መስፋፋት እና ለአካባቢው ነዋሪዎች በአግባቡ ካልተዳረሰው የሴፍቲ ኔት መርሃ-ግብር ጋር ተዳምሮ ሥራ አጥነት እንዲስፋፋ እና ድኅነት ሥር እንዲሰድ ምክንያት መሆኑንም ጥናቱ አሳይቷል፡፡

ጥናቱ የተባበሩት መንግስታትን የ 2021 ሪፖርት ዋቢ አድርጎ እንዳመላከተው ÷ በችግሩ ሴቶች ይበልጥ ተጠቂ እንደሆኑና በኑሮ ውድነት ምክንያት በርካቶች ምግብን ጨምሮ መሠረታዊ የሚባሉትን የዕለት ተዕለት አቅርቦቶች ለማግኘት ቅንጦት ሆኖባቸዋል፡፡

በቀጠናው በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች ÷ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ውድመት እንዲደርስ እና አርሶ አደሮች እንዳያመርቱ ፣ ካመረቱም ወደ ገበያ እንዳያቀርቡ እክል እንደሚፈጥሩ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

እንደ “ኬር” ጥናት ÷ በአካባቢዎቹ በቤት ውስጥ ያለውን የምግብ አቅርቦት የማሟላት ፣ የመገበያየት እና የማብሰል ሥራ በአብዛኛው በሴቶች እና ልጃገረዶች ጫንቃ ላይ የወደቀ በመሆኑ የመጀመሪያዎቹ የችግር ገፈት ቀማሽ ይሆናሉ ነው የተባለው፡፡

ጥናቱ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በሱዳን ያለውን ልማድ ጠቅሶ ሴቶች ባሎቻቸውን እና ልጆቻቸው ከመገቡ በኋላ ጥቂት ከእነሱ የተረፈውን እንደሚመገቡ እና በቤታቸው ከውሳኔ ሰጪነት የተገለሉም መሆናቸውን ይፋ አድርጓል፡፡

ጥናቱ ሁኔታውን በቁጥር ሲያስደግፈውም 82 በመቶ ያህሉ የሱዳን ሴቶች አንዳንዴ ምግብ ሳይመገቡም ቢሆን ቤታቸውን ያለወንዶች ድጋፍ ያስተዳድራሉ፡፡

በወንዶች ድጋፍ ቤታቸውን ከሚመሩ ሴት ሱዳናውያን ደግሞ 56 በመቶ ያህሉ ለባለቤታቸው አና ለልጆቻቸው በቂ ምግብ ለማቅረብ ሲሉ አንዳንዴ ምግብ ሳይመገቡ ይውላሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.