Fana: At a Speed of Life!

የሮቤ – ጋሴራ – ጊኒር የመንገድ ስራ ግንባታ መዘግየቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሮቤ – ጋሴራ – ጊኒር የመንገድ ስራ ፕሮጀክት በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በመስክ የስራ ቅኘት ተገመገመ።

በዚህ ወቅት የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ፣የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን  ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘ፣ የኢመባ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የክልልና የዞኑ አመራሮች ተገኝተዋል።

የተቋማቱ መሪዎች ከአካባቢውዎቹና ከዞኑ ከተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ጋርም ምክክር አካሂደዋል።

የሮቤ – ጋሴራ – ጊኒር የመንገድ ስራ ፕሮጀክት አሁናዊ ሁኔታና በእስካሁኑ አፈጻጸም የተሰሩ ስራዎች ያግጠሙ ችግሮችና ቀጣይ የስራ እቅዶችን በተመለከተ ግምገማም ተካሂዶል።

በሁለት ምዕራፎች የሚገነባው የሮቤ – ጋሴራ – ጊኒር የመንገድ ስራ ፕሮጄክት ሲጠናቀቅ የ121 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው ተብሏል፡፡

ይህም ከሮቤ ጋሴራ 60 ኪሎ ሜትር ሲሆን ከጋሴራ ጊኒር ደግሞ 60 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመትን ይሸፍናል።

የመጀመሪውን ፕሮጀክት ግንባታ የሚያከሂዱት አፍሮጽዮን ኮንስትራክሽን ከራማ ኮንስትራክሽን ጋር በጋራ ነው።

በተደረገው የፕሮጀክት አፈጻጸም ግምገማም መከናወን ከነበረበት አኳያ የዘገየ መሆኑ ነው የተገለፀው።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን  ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘ የአፈጻጸም ድክመቱን በፍጥነት አስተካክሎ የመንገድ ግንባታውን እንዲከናወን የመጨረሻ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

በስፍራው የተገኙት የራማ ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ፍሬው ተድላ ድርጅታቸው ፕሮጀክቱን ከአፍሮ ጽዮን ተቋራጭ ጋር በጋራ የወሰደው በመሆኑ ችግሮች እንዳሉበት አምነው፣ የህዝብን ቅሬታ ለመፍታት ተቋራጫቸው ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

የግንባታ ፕሮጀክቱ በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ስር ያለው ሁለተኛውን ምዕራፍ ማለትም ከጋሴራ ጊኒር የሚወስደውን መንገድ እጅግ መዘግየቱ ተገምግሟል።

በተደጋጋሚ ድጋፍና ክትትል ቢደረግም አፈጻጻሙ ሊሻሻል አለመቻሉም የስራ ሀላፊዎቹ በመስክ ምልከታ ጭምር ማረጋገጣቸው ነው የተገለፀው።

በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጉልህ አፈጻጸም ማሳየት ካልቻለ መንግስት አፍጣኘ የመፍትሄ እርምጃ እንደሚወስድም የስራ ሃላፊዎቹ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ የመስክ ቅኝቱ መሰረታዊ አላማ ህዝቡ የሚያነሳውን ቅሬታ አዳምጦ ላልተገባ ቅሬታ ምክንያት የሆኑ የስራ ተቋራጮች ላይ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ነው ብለዋል።

መንግስት መዋዕለ ነዋይ መድቦ ድጋፍና ክትትል እያደረገም ለዘመናት የቆየ የህዝቦችን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ ፕሮጀክትን በማጓተት ህዝብን ቅሬታ ውስጥ የሚከቱ ድርጅቶችን እንደማይታገስ መግለፃቸውን ከባለስልጣኑ ያገኘኘው መረጃ ያመለክታል።

የስራ ሃላፊዎቹ የጀመሩትን የተጠናከረ የመስክ ቅኝትና ግምገማ አጠናክረው በመቀጠል ችግር ያለባቸውን ፕሮጀክቶች እንዲታረሙ በማድረግ የሀገሪቱ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ እንዲፋጠን እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.