Fana: At a Speed of Life!

የሰላም ሚኒስቴር 12 የእርሻ ትራክተሮችን ለክልሎች አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰላም ሚኒስቴር በ28 ሚሊየን ብር የገዛቸውን የእርሻ ትራክተሮች ለጋምቤላና ለቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች አስረከበ።

በሰላም ሚኒስቴር የፌደራሊዝምና የልዩ ድጋፍ ጀኔራል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ደገፋ ቶሎሳ፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎችና የአርብቶ አደር አካባቢዎች ልዩ ድጋፍ መስጠትና ሌሎች የፌደራል መስሪያ ቤቶች የሚሰጡትን ልዩ ድጋፍ ማስተባበር ከተሰጡት ተልዕኮወች አንደኛው መሆኑን አንስተዋል።

የዚህ የልዩ ድጋፍ ማዕቀፍ ለሆኑት አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና ለጋምቤላ በየዓመቱ 450 ሚሊየን ብር መድቦ በሰላም ሚኒስቴር በኩል የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ እያደረገ ይገኛልም ነው ያሉት።

በዚህም 12 የእርሻ ትራክተሮች ለጋምቤላና ለቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የተረከቡ ሲሆን፥ ግብርናን በማዘመን፣ አርሶ አደሮቹን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር እንዲላመዱ በማድረግ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስረፅ ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አንስተዋል።

ከጋምቤላና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የተወከሉ የስራ ሃላፊዎች በበኩላቸው በሁለቱ ክልሎች ሰፊና ሊለማ የሚችል መሬት እንዳለ ገልፀዋል።

ትራክተሮቹ በክልላቸው የሚገኙ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ እርሻ ስራ እንዲሰማሩና የልማት ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ከፍ ያለ ሚና እንዳላቸው መናገራቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.