Fana: At a Speed of Life!

የሰላም ሚኒስትር ዲኤታዋ ከዓለም አቀፉ የወጣቶች ህብረት መስራች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን ከዓለም አቀፉ የወጣቶች ህብረት መስራች ዶክተር ኦክ ሶ ፓርክ ጋር ተወያዩ።

ሚኒስትር ዲኤታዋ በውይይታቸው ብሄራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም በማዘጋጀት ወጣቱን የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቆ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።

አያይዘውም ከዚህ በፊት በዓለም አቀፉ የወጣቶች ህብረት አማካኝነት የተሰጡ የአስተሳሰብ ለውጥ ስልጠናዎች ወጣቶች መልካም አስተሳሰብ በመያዝ ሃገራቸውን እንዲያገለግሉ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ተቋሙ በብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም በሚሰጠው ስልጠና ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ ስልጠናን በማካተት ከዓለም አቀፉ የወጣቶች ህብረት ጋር ለመስራት ማሰቡን ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ የወጣቶች ህብረት መስራች ዶክተር ኦክ ሶ ፓርክ በበኩላቸው፥ ህብረቱ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር አብሮ ለመስራትና ተቋሙን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።

ወጣቶች የልማት ሀይል በመሆናቸው የሰላም ባለቤት እንዲሆኑ የአስተሳሰብ ለውጥ ስልጠናዎች አስፈላጊ በመሆናቸው ስልጠናዎችን ለመስጠት ፈቃደኛ ነን ብለዋል።

በውይይታቸው የሰላም ሚኒስቴር ወጣቶች በስነ ምግባር ታንፀው ሃገራቸውን የሚያገለግሉ ዜጎች እንዲሆኑ ስራዎች እየሰራ እንደሆነ መገለጹን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.