Fana: At a Speed of Life!

የሰሜን ዕዝን የሬዲዮ መገናኛ በመጥለፍ የተጠረጠሩ 7 የጄኔራል መኮንኖች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ገብረመድህን ፍቃዱን ጨምሮ ሃገርን በመክዳት ወንጀልና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለመናድ በማሰብ ወንጀል የተጠረጠሩ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
የመከላከያ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ገብረመድህን ፍቃዱ፣ የመከላከያ ሰራዊት ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይርዳው ገብረመድህን፣ የደቡብ ዕዝ ሰው ኃብት ልማት አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ገብረዮኃንስ ሳርሲኒዮስ፣ የሰሜን ዕዝ መረጃ ዘርፍ ኃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል ኢንሱ ኢጳጆ ረሾን ጨምሮ ሰባት ሀገርን በመክዳት ወንጀልና ህገመንግስትና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ ማሰብ ወንጀል በቁጥጥር ስር ውለው በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡
የፌደራል ፖሊስም ተጠርጣሪዎቹ መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው መቀመጫውን ትግራይ ክልል ካደረገ የፀረ ሰላም ቡድን ከፍተኛ አመራሮች ተልዕኮ በመቀበል በመከላከያ ጦር ውስጥ ሴሎችን በማደራጀት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ የሰሜን ዕዝ ሬዲዮ ግንኙነት ማቋረጣቸውን ገልጿል፡፡
በዚህም ሰራዊቱ እርስ በርስ እንዳይገናኝና እንዳይቀላቀል፤ በጦሩ ላይም የሞት፣ የአካል ጉዳትና የጦር መሳሪያ ዝርፊያ እንዲፈፀም አድርገዋልም ነው ያለው፡፡
እንዲሁም በሀገር ውስጥና ከውጭ የሚቃጣበትን ጥቃት እንዳይከላከልና የሰሜን ዕዝ ጦር እንዲፈርስ በማድረግ በተቀናጀ መልኩ ኦነግ ሸኔ ከተባለና ከሌሎች የፀረ ሰላም ሃይሎች ጋር በመተባበር በተለያዩ ክልሎችም ሐይማኖትን ሽፋን አድርገው የብሄር ግጭት በማስነሳትም ሀገርን ለመበተን ሲሰሩ እንደነበር መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱም የወንጀሉን ክብደትና በሀገር ደህንነት ላይ ከባድ ጉዳት የሚያደርስ ወንጀል መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ለፖሊስ 14 የምርመራ ቀን ፈቅዷል፡፡
በታሪክ አዱኛ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.