Fana: At a Speed of Life!

የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ እና የኦክስጅን እጥረት እያጋጠመ ስለሆነ ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠንቀቅ ያስፈልጋል- ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከቀን ወደ ቀን በመላው ሀገሪቱ  በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመያዝ ምጣኔ ፤ ህይወታቸውን የሚያጡ እና የፅኑ ህክምና አገለግሎት የሚፈልጉ ታካሚዎች ቁጥር አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢነስቲትዩት አስታወቀ።

በትላንትናው ዕለት 30 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ቫይረስ ህይወታቸውን አጥተዋል ያለው ኢንስቲትዩቱ  ይህ ቁጥር ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ ጀምሮ የመጀመሪያው ከፍተኛ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል ብሏል።

በመጋቢት 3 – 4 ቀን 2013 ፤ በሁለት ቀን ብቻ 57 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በአጠቃላይ 2 ሺህ 540 ግለሰቦች በኮቪድ-19 ህይወታቸውን አጥተዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 74 በመቶ የሚሆኑት ከህክምና ማዕከላት ሲሆን 24% ከአስክሬን ላይ ናሙና ተወስዶ ተመረመረበት ወቅትመሆኑ  ተነግሯል።

በተጨማሪም 1 በመቶ ድርሻ የሚወስደው ደግሞ የቤት ውስጥ ውሸባ እና እንክብካቤ ወቅት ተገቢውን የህክምና ባለሙያ ምክር ባለመተግበር ህይወታቸውን ያጡ ግለሰቦች ቁጥር ነው።

እስካሁን ከፍተኛ የሞት ቁጥር ያስመዘገቡ ክልሎች :-

አዲስ አበባ ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ 1 ሺህ 852 ግለሰቦች ወይም 73 በመቶ

ኦሮሚያ ክልል 256 ግለሰቦች ወይም 10 በመቶ

በአማራ ክልል 105 ግለሰቦች ወይም 4 በመቶ

በሲዳማ ክልል 75 ግለሰቦች ወይም 3 በመቶ ግለሰቦች ህይወታቸውን አጥተዋል።

በኮቪድ-19 በትላንትናው ዕለት ለ 7 ሺህ 654 ግለሰቦች ናሙና የሰጡ ሲሆን 1 ሺህ 483 ግለሰቦች የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል ።

ይህ ማለት ከተመረመሩት 100 ግለሰቦች 19 ያህሉ ወይም 19 በመቶ ኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።

የኮቪድ-19 ቫይረስ በየትኛውም ቦታ ፤ በማንኛውም የዕድሜ ክልል እና ፆታ ሳይመርጥ የሚይዝ እና ህይወት የሚያሳጣ ስለሆነ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ነው ኢንስቲቱዩቱ አሳስቧል።

የህክምና ማዕከላትም መስራት ከሚችሉት አቅም በላይ እየሆነ ስለመጣ ፤  የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ እና የኦክስጅን እጥረት እያጋጠመ ስለሆነ ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የመጀመሪያው የኮቪድ19 ታማሚ በሃገሪቱ  መገኘት በተረጋገጠበት በአንድ ዓመቱ በመላ ሀገሪቱ የኮቪድ19 ክትባት በትላንትናው ዕለት መስጠት መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

የመጀመሪያዎቹን አስከፊ ትንበያዎች ሳይደርሱ ለዚህ ምዕራፍ መድረስ ትልቅ ስኬት በመሆኑ በመስዋትነት እያገለገሉ የሚገኙትን የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች እንዲሁም አመራሮች ፣ በጎ ፈቃደኞች እና መላው ማህበረሰቡ  የተከሰተው ወረርሽኝ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

ሆኖም ትናንት ከፍተኛውን የኮቪድ19 ሞት ቁጥር መመዝገቡን በመግለፅ ወረርሽኙ አሁንም እጅግ አሳሳቢና ስጋት ሆኖ እንደቀጠለ በመሆኑ የመከላከያ እርምጃዎችን በማክበር የምንወዳቸውን እና እራሳችንን ለመጠበቅ የጋራ ሀላፊነታችንን እንወጣ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.