Fana: At a Speed of Life!

የሱዳን ሰራዊት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፈጸመውን ወረራ በመቀልበስ ወደ ቀደመ ይዞታው መመለስ ይገባዋል- አምባሳደር ይበልጣል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 5 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የብሔራዊ ድንበር ኮሚሽን በዛሬው ዕለት ተቀማጭነታቸው በሱዳን ለሆኑ ዲፕሎማቲክ ሚሽኖች፣ ቆንስላዎች እና የዓለምአቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ገለፃ አድርጓል።

መድረኩ ላይ የተገኙት በሱዳን የኢ.ፌ.ድ.ሪ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ ባሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች እና የጋራ የድንበር መድረኮች አማካኝነት በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በዚህ ረገድ ከዳግልሽ ተራራ በስተሰሜን ከሰፈራ እና ከእርሻ መሬት ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ሁለቱን ሀገራት የሚያስማማ የመፍትሔ ሃሳብ እንዲመጣ የሚደነግገው እና በሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በፈረንጆቹ ሐምሌ ወር 1972 የተደረገው የማስታወሻ ልውውጥ ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው እንደሆነ በአጽንኦት አስረድተዋል።

አያይዘውም በ1972ቱ የማስታወሻ ልውውጥ በተቀመጠው መሰረት የጉዊን መስመርን ዳግም ማካለል ከመጀመሩ በፊት ከዳግልሽ ተራራ በስተሰሜን ከእርሻ መሬት እና ሰፈራ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ ልዩ ኮሚቴው ሁለቱን ሀገራት የሚያስማማ የመፍትሔ ሃሳብ ያካተተ ሪፖርት ለጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ማቅረብ እንደሚኖርበት ገልጸዋል።

ምንም እንኳ የጋራ ልዩ ኮሚቴው ሁለቱን ሀገሮች የሚያስማማ የመፍትሔ ሃሳብ ለማቅረብ ስምንት ዙር ስብሰባዎችን ቢያካሂድም ኃላፊነቱን ገና እንዳላጠናቀቀ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ የኢትዮጵያ-ሱዳን ድንበር የጋራ ልዩ ኮሚቴ ስራ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጥቅምት ወር መጨረሻ ህግ ለማስከበር ወደ ትግራይ ክልል ያደረገውን ስምሪት እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀሙን አንስተዋል።

በዚህ መሰረት የሱዳን ሰራዊት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ በመግባት ንብረት ከመዝረፉ፣ ወታደራዊ እና የእርሻ ካምፖችን ከማቃጠሉ ባሻገር በኢትዮጵያውያን ላይ እስራት፣ ጥቃት እና ግድያ መፈጸሙ እንዲሁም በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ማፈናቀሉን ጠቅሰዋል።

ይኸውም የ1972 የማስታወሻ ልውውጥን በግልጽ የጣሰ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።

አምባሳደሩ አክለውም በሁለቱ እህትማማች ሀገራት ጸንቶ ከቆየው አጋርነት እና ትብብር መንፈስ በተቃረነ መልኩ አጋጣሚውን በመጠቀም የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት ለቋቸው የወጣ ካምፖችን መቆጣጠሩን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ በተጨማሪም ሱዳን በችግር ውስጥ በነበረችበት ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያ ከሱዳን ህዝብ ጎን መቆሟን አውስተው፣ ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይዋ በተጠመደችበት ወቅት ከሱዳን ሰራዊት የደረሰባት ጥቃት የሚገባት እንዳልነበረ መግለፃቸውን ከኤምባሲው ያገኘኘው መረጃ ያመለክታል

አምባሳደሩ በገለጻቸው አክለውም የማስተካከያ እርምጃ በፍጥነት ካልተወሰደ፣ ታይቶ የማይታወቀው የሱዳን ሰራዊት ተግባር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ብሎም የጋራ ድንበሩን ዳግም የማካለሉን ስራ የሚያወሳስብ እና ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች እንዲሁም ለቀጠናው ከፍ ያለ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚኖረው መሆኑን አንስተዋል።

አምባሳደሩ የኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ልዩነቱን ሁለቱ ሀገራት በገቧቸው ስምምነቶች እና ባሉ የጋራ የድንበር መድረኮች መሰረት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

አምባሳደሩ አክለውም ለችግሩ ዘላቂ እልባት ለመስጠት፡ አንደኛ፣ የሱዳን ሰራዊት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፈጸመውን ወረራ በመቀልበስ በ1972ቱ የማስታወሻ ልውውጥ በተቀመጠው መሰረት ወደ ቅድመ-ህዳር 2020 እንዲመለስ፣

ሁለተኛ፣ ወደ ድንበር ዳግም ማካለል ከመገባቱ በፊት የጋራ ልዩ ኮሚቴው በ1972 የማስታወሻ ልውውጥ መሰረት ከዳግሊሽ ተራራ በስተሰሜን ከሰፈራ እና እርሻ መሬት ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ሁለቱን ሀገራት የሚያስማማ የመፍትሔ ሃሳብ የማቅረብ ስራውን እንዲያጠናቅቅ፣

ሶስተኛ፣ የጋራ ድንበሩን ዳግም ለማካለል ሁለቱ ሀገራት ያቋቋሟቸው የጋራ የድንበር ኮሚሽን፣ የጋራ የቴክኒክ የድንበር ኮሚቴ፣ እና የጋራ ልዩ ኮሚቴ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እና ስራቸውን እንዲያጠናቅቁ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.