Fana: At a Speed of Life!

የሱዳን ጦር እና የቀድሞ የደህንነት ሃይሎች ተጋጩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሱዳን ጦር እና የሱዳን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ታማኝ ናቸው የተባሉ የደህንነት ሃይሎች ተጋጩ።

የቀድሞ የደህንነት አካላት በሰሜናዊ ካርቱም ከባድ መሳሪያዎችን መተኮሳቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ከአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ የሚገኝን የደህንነት መስሪያ ቤት ህንጻም ተቆጣጥረዋል ተብሏል።

የሱዳን ወታደራዊ ምንጮች ደግሞ የመንግሥት ወታደሮች በተቀናቃኞቻቸው የተያዙትን ህንጻዎች መልሰው መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።

በተኩስ ልውውጡ አምስት ሰዎች መቁሰላቸውም ነው የተነገረው።

የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት የቀድሞ የደህንነት ሰዎች በሃገሪቱ መረጋጋት እንዳይሰፍን እያደረጉ ነው በሚል ይወነጅላቸዋል።

አሁን ላይ በሃገሪቱ ለሚስተዋለው አመጽና አለመረጋጋትም የቀድሞው የደህንነት ሃላፊ ሳላህ ጎሽ አስተዋጽኦ አድርገዋልም ነው ያለው።

የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊ የሆኑት ጀኔራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ፥ ድርጊቱን እንደማይታገሱ ተናግረዋል።

አሁን ላይ በሃገሪቱ እየታየ ያለው ሰላምና መረጋጋት የሃገሪቱ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ከስልጣን ከወረዱ በኋላ የተካሄደውን ማሻሻያ ሲቃወሙ በነበሩ አካላት ፈተና ሊገጥመው ይችላል የሚል ስጋትም አጭሯል።

ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ተቃውሞዎችን ሲመሩ የነበሩ አካላት መሰል ኃላፊነት የጎደላቸው ተግባራት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ምንጭ፦ ቢ.ቢ.ሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.