Fana: At a Speed of Life!

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለፈው በጀት ዓመት በማህበሰብ አቀፍ ተግባራት የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ።

ድርጅቶቹ ኮሮናን ለመከላከልም ከ800 ሚሊየን ብር በላይ የዓይነት ድጋፍ ማድረጋቸው ተነግሯል።

ባለፈው በጀት ዓመት በአገሪቱ የሚገኙ የሲቪል ማኅበራት በግብርና፣ በጤና፣ በአካባቢ ልማትና፣ በሰብዓዊ ድጋፍ የተለያዩ ተግባራትን አከናውነዋል።

ይህንን ያሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የምዝገባ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ወርቁ ናቸው።

እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ አገር አቀፍ እንቅስቃሴዎች ማኅበራቱ የተሳተፉባቸው ተግባራት መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፥ ኮሮናን ለመከላከል የተደረገውን ጥሪ በመቀበል በመጀመሪያው ዙር ብቻ ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

እንደ ሀገር ኮሮናን የመከላከል ጥረትን ለማገዝ ማህበራቱ በብርና በዓይነት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ነው አቶ ተሾመ የገለጹት።

ጾታዊ ጥቃትን የተመከለከቱ ሪፖርቶችም በማኅበረሰቡ መነቃቃት መፍጠራቸውን ጠቅሰው÷ በሲቪል ማህበራቱ የተከናወኑት ተግባራት የተሻለ አፈጻጸም ማሳየታቸውን አስረድተዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ፎረም የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ንጉሱ ለገሰ በበኩላቸው፥ ማህበራቱ ከዚህ በፊት ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ሰላምን ለመፍጠር ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን የማረጋጋት ስራዎች ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

ኮቪድ 19 ከመከሰቱ በፊት ማህበራቱ በተናጠል በአካባቢ ጥበቃ፣ በውሃ ማውጣት፣ በትምህረት ቤት ግንባታ፣ በጤናው ሴክተር ድጋፍና በተለያዩ ልማት ነክ ስራዎች ላይ መሳተፋቸውን አስረድተዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ደግሞ የግንዛቤ ማስጫበጫ ተግባራትና የድጋፍ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው÷ በአምስት ቋንቋ የተሰራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርታዊ ቪዲዮ መሰራጨቱንም ተናግረዋል፡፡

ግብረኃይል በማቋቋም ለኮሮና መከላከል የሚውል በዓይነት ከ800 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ በመላ አገሪቱ መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል የሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩ ተግበራትን ለማከናወን ፈታኝ ሁኔታዎች እንደጋጠማቸውና በቀጣይ ከሲቪል ማህበራቱ በሚጠበቅ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ወጣቱን ከጥፋት ለመታደግም በቀጣይ በሰላምና መረጋጋት ላይ ሲቪል ማህበራቱ በዋነናት እንደሚሰሩ ዶክትር ንጉሱ ጠቁመዋል፡፡

ማህበራቱ እነዚህን ተግባራት እያከናወኑ ቢሆንም የአቅም ውስንነት፣ የገንዘብ እጥረት፣ የራስን የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ጥረት አለማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውንም ነው ዶክተር ንጉሴ የጠቀሱት።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ2ሺ 500 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተመዝግበው እንደሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.