Fana: At a Speed of Life!

የሲቪክ ማህበረሰቡ የህዝቦች በጎ እሴቶች እንዲጎለብቱ መስራት እንዳለባቸው ጠ/ሚ ዐቢይ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሲቪክ ማህበረሰቡ የህዝቦች በጎ እሴቶች እንዲጎለብቱ መስራት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በዛሬው እለት ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይም ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሁሉም አካላት ተሳትፎ ስለሚያስፈልግ የሲቪክ ማህበረሰቦች በሰብአዊ ልማት ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ጠይቀዋል።

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች፥ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሻሻል ስራቸውን ከቀደመው ጊዜ በተሻለ መልኩ ለማስኬድ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።

ሆኖም የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ከህግ ማሻሻያ ባለፈ በሲቪክ ማህበረሰቡ እና በመንግስት መካከል የተጠናከረ ትብብር መፍጠር ይገባል ብለዋል።

እቅድ ከማውጣት ጀምሮ ዜጎችን የሚጠቅሙ ስራዎች ሲሰሩ የሲቪክ ማህበረሰቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባም አንስተዋል።

ለዓመታት የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲዳከሙ በህግ ጭምር ሲሰራበት ቆይቷል ያሉት ተሳታፊዎቹ፥ መንግስት አሁን ላይ ድርጅቶቹ ተጠናክረው እንዲወጡ ሊደግፋቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በበኩላቸው፥ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መጠናከር ለዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ በለውጡ ማግስት አስቀድሞ ከተሰሩ ስራዎች መካከል የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሻሻል እንደሆነ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲፈጠር የሚፈለገው የሲቪክ ማህበረሰብ በከተሞች የታጠረ ሳይሆን ወደ ሁሉም አካባቢዎች ወርዶ የሚሰራ ሊሆን እንደሚገባው አንስተዋል።

ጠንካራና ሙያውን የሚያከብር የሲቪክ ማህበረሰብ መፍጠር ከተቻለ የኢኮኖሚ ትርፍ እና የፖለቲካ ትርፍ በሚፈልጉ ሀይሎች መካከል ሚዛን አስጠብቆ ለህዝቦች ተጠቃሚነት መስራት እንደሚቻልም ነው ያስታወቁት።

የሲቪክ ማህበረሰብ ከየትኛውም ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ ለህዝቦች ተጠቃሚነት ብቻ እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

በአላዛር ታደለ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.