Fana: At a Speed of Life!

የሲቪክ ማህበራት ለመጪው ምርጫ ማህበረሰቡን የማንቃት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል-ምሁራን

አዲስ አበባ፣ጥር 12፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲቪክ ማህበራት ለመጪው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ማህበረሰቡን የማንቃት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ።

ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስተያየታቸውን የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካ ሳይንስ መምህር ዶክተር ደመቀ አጪሶ፥ መጪው ምርጫ ተአማኒ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን የዜጎችን ሰላም ማስከበር ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።

ማህበረሰቡ የዜጎችን ሰላም የሚያውኩ ድርጊቶችን ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ አለበት ያሉት ዶክተር ደመቀ፥ የጸጥታ አካላትም ተገቢው ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው አንስተዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ አሻግሬ በበኩላቸው፥ ዜጎች በምርጫ ሂደት ላይ የሚከናወኑ የሃሳብ ፍጭቶችን ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መገንዘብ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

ለዚህም በሀገሪቱ የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት ዜጎች ስለ ምርጫ ያላቸውን ግንዛቤ የማስፋት ስራ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያሰራጯቸውን መረጃዎች በትክክለኛ እና በሚመለከታቸው አካላት ማስተላለፍ ያለባቸው መሆኑንም አንስተዋል።

ዜጎች መረጃዎችን በጥንቃቄ ማዳመጥ እና በሰከነ መልኩ መረዳት ይጠበቅባቸውል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ፥ በምርጫው ምህዳር የሚገቡ አካላት የያዟቸውን ፕሮግራሞችና አላማዎች በሚገባ ሊያጤኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በቅድመ ምርጫም ሆነ በምርጫው ወቅት ህዝቡን የማንቃት ሃላፊነት ያለባቸው የሲቪክ ማህበራትም፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲያቸውን እና ፕሮግራማቸውን የሚያጋሩበት መድረክ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

ከለውጡ በኋላ የሲቪክ ማህበራት የሚሰሩበት ህግ መሻሻልን እንደ ጥሩ መንደርደሪያ የሚያነሱት ፕሮፌሰሩ፥ በመጪው ምርጫ ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያመች ምህዳር መኖሩን አንስተዋል።

በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ወርቁ ያዕቆብ፥ የሲቪክ ማህበራት መሰረታዊ የፍትሃዊነት መርሆችን ጠብቀው ለሁሉም የምርጫ ተሳታፊዎች እኩል ምህዳርን ሊከፍቱ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተኣማኒ፣ ፍትሃዊ፣ አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን ህብረተሰቡም ሆነ የሲቪክ ማህበራት በንቃት እንዲሳተፉ ምሁራኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በሃይለኢየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.