Fana: At a Speed of Life!

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር የ1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ማካሄድ ጀምሯል።
 
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ በጉባኤው መክፈቻ ላይ በህልውና ዘመቻው ላይ የክልሉ ህዝብ ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበር ተናግረዋል።
 
የክልሉ ህዝብ ለሀገሩ ሉዓላዊነት ልጆቹን መርቆ ከመስጠት በተጨማሪ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የተለያዩ ድጋፎችን አድርጓል ብለዋል።
 
ጉባኤው ለሶስት ቀናት እንደሚካሄድ የምክር ቤቱ አፈጉባዔ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ ተናግረዋል።
 
በጉባኤው ላይ የክልሉ የ10 ዓመት መሪ እቅድ ቀርቦ ፀድቋል።
 
የክልሉ ፕረስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፊሊጶስ ናሆም በ10 ዓመት መሪ እቅድ መሰረት ክልሉን በሁሉም ዘርፎች ለማሻገር በትኩረት እንደሚሰራ በጉባኤው ላይ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
 
በግብርናው ዘርፍ አርሶ አደሮች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘዉ በማምረት ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉና በምግብ ዋስትና እራሳቸውን እንዲችሉም ይሰራልም ነው ያሉት።
 
ዘመናዊ የመስኖ እርሻም እንዲስፋፋ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
 
የወጣቶች ስራ አጥነት ለመቀነስ ወጣቶች በተገኘው እድል ሁሉ ተጠቅመው ስራ እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰራም ተመልክቷል።
 
በክልሉ የወጣቶች ስራ አጥነት 20 በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ በ10 ዓመቱ መሪ እቅድ በእነዚህ ዓመታት ወደ 7 በመቶ ለማውረድ እንደሚሰራ በምክር ቤቱ ከስምምነት መደረሱን አቶ ፊሊጶስ ተናግረዋል።
 
በትምህርትና ጤና ዘርፎችም ላይ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር መቅረፍ በዚህ መሪ እቅድ ትኩረት እንደተሰጠው ተመልክቷል።
 
መደበኛ ጉባዔው የሶስቱን የመንግስት አካላት የ2014 ዓ.ም. እቅድና የምክር ቤቱን የሥነ-ምግባር ደንቦች መርምሮ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።
 
እንደዚሁም የቋሚ ኮሚቴና የጎደሉ የካቢኔ አባላትን ሹመት ያፀድቃል ተብሎ እንደሚያፀድቅም ነው የሚጠበቀው።
 
 
 
በቢቂላ ቱፋ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.