Fana: At a Speed of Life!

የስልጤ ዞን ነዋሪዎች በሃይማኖት ሽፋን የአብሮነት እሴቶችን ለመሸርሸር የሚሰሩ አካላትን አወገዙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በስልጤ ዞን በሃይማኖት ሽፋን ለዘመነት የኖሩትን አብሮነትና የመቻቻል እሴቶችን ለመሸርሸር የሚሰሩ አካላትን በጽኑ እንደሚያወግዙ የዞኑ ነዋሪዎች ገለጹ።

በዞኑ በሁሉም ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር በወቅታዊ ሀገራዊና ከባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

በዚህ ወቅት ሰሞኑን በስልጤ ዞን ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የተከሰተው ክስተት የስልጤን ህዝብ የማይወክልና የሚወገዝ መሆኑን አንስተው፥ ለውጡን ለማደናቀፍና ሀገር ለማፍረስ ከጠላቶቻችን ተልዕኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አክራሪና ጽንፈኛ ሃይሎችን ለመመከት በየደረጃው ያለው አመራርና መላው ህብረተሰብ ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበትም አንስተዋል።

የስልጤ ብሔረሰብ ጥንትም ሆነ ዛሬ ሰላምና ልማት- ወደድ ህዝብ ብሔር ፣ዘር ፣ቀለም ፣ ሃይማኖት ሳይል ለዘመናት አብሮና ተቻችሎ የኖረውን ማህበረሰብ እሴት ለመሸርሸርና በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በመደነቀፍ የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚንቀሰቀሱ ኃይሎችን ነቅቶ መጠበቅና መመከት አለበት ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

ለዘመናት ተቻችለው፣ ተከባብረውና ተደጋግፈው በሚኖሩ ሙስሊምና ክርስቲያን ህብረተሰቦች መካከል ፀብ በማጫር በሃይማኖት ሽፋን እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም የገቡ ኃይሎች ሴራ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ማክሸፍ የተቻለ መሆኑንም በውይይቱ ተገልጿል።

ጠላቶች በሸረቡት ወጥመድ በየአከባቢው የሚፈበረኩ የግጭት ማስነሻ አጀንዳዎችን በጥንቃቄ በመፈተሽና በመለየት ተገቢውን እልባት በመስጠና ለውጡን ለማስቀጠል መላው የዞኑ ህዝብ በጋራ ትብብር መስራት እንዳለበትም ነው የተጠየቀው።

በዕለቱም በዞኑ የተፈጠራውን የጸጥታ ችግር ከማክሸፍ በተጨማሪ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ልማታዊ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዲችሉ የታቀዱ የዘጠና ቀን ተግባሮች ዙሪያም ውይይት መደረጉን ከዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.