Fana: At a Speed of Life!

የስሎቬኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን መልቀቃቸውን አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የስሎቬኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርያን ሳሬች ስልጣን መልቀቃቸውን አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ መልቀቂያቸውን ለሃገሪቱ ፓርላማ ያስገቡ ሲሆን፥ ጠቅላላ ምርጫ እንዲካሄድም ጥሪ አቅርበዋል።

እርሳቸው የሚመሩት ጥምር ፓርቲ በፓርላማው አቅም እያጣ መምጣት ለመልቀቃቸው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ፓርቲው በፓርላማው የውሳኔ ሃሳብ ለማሳለፍ መቸገሩ ህዝቡ ከመንግስታቸው የሚጠብቀውን ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ ያደርገዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ አሁን ባለው ሁኔታ የህዝቡን ፍላጎት ማሟላት አልችልም ብለዋል።

ከዚህ አንጻርም በሃገሪቱ የህዝቡን ፍላጎት ባማከለ መልኩ ጠቅላላ ምርጫ እንዲካሄድ ለፓርላማው ባስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ ጠይቀዋል።

በፈረንጆቹ 2018 አምስት ግራ ዘመም ፓርቲዎች ጥምር መንግስት መመስረታቸው ይታወሳል።

ጥምር ፓርቲው በፓርላማው ካለው 90 ወንበር 43 መቀመጫዎችን ብቻ አሸንፏል።

አሁን ላይ በፓርላማው አብላጫ መቀመጫ ያለው የስሎቬኒያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ አዲስ መንግስት ለመመስረት ጥረት ሊያደርግ ይችላል እየተባለ ነው።

ፓርቲው ጥምረት ሳይመሰርት በፓርላማው 26 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፥ ጥምረት ከመሰረተ አዲስ መንግስት የማቋቋም አቅም አለው ተብሏል።

ይህ የማይሳካ ከሆነ ግን ምርጫው ሊካሄድ ይችላል ነው የተባለው።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ብሎ የሃገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር አንድሬህ ቤርቶንሴልጅ ስልጣን መልቀቃቸውን የሃገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

ምንጭ፦ አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.