Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል ቆላማ አካባቢ ልማት ፕሮጀክት ከ50 በላይ የልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ማድረጉን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ቆላማ አካባቢ  ልማት ፕሮጀክት በ2014 በጀት አመት ከ50 በላይ የልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ማድረጉን ገለጸ፡፡

በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን ሰብሳቢነት የሚመራው የክልሉ ቆላማ አካባቢና ተፋሰስ ልማት ስራ አመራር ቦርድ÷ የቆላማ አካባቢዎች ልማት ፕሮጀክት የመጀመሪያውን የ10 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

ቦርዱ ፕሮጀክቱ በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮች ህይወት ላይ ያመጣውን ለውጥና በፕሮጀክቱ ስራ አፈፃፀም ላይ የታዩ ክፍተቶችን ገምግሟል።

በሶማሌ ክልል ቆላማ አካባቢ ልማት ፕሮጀክት በበጀት አመቱ በተለያዩ የክልሉ ገጠር አከባቢዎች ከ50 በላይ የሚሆኑ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በ138 ሚሊየን ብር መተግበራቸውና ለአገልግሎት መብቃታቸው ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች የሚኖሩ ከ4 ሺህ በላይ ወጣቶችን በግብርና፣ በእንስሳት እርባታ፣በማር ምርት እንዲሁም በጥቃቅን እና በሌሎች የሥራ መስኮች ማሰማራቱ እና የስራ እድል መፍጠሩ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

36 የሰው ጤና ማዕከላትን፣13 የእንስሳት ህክምና መስጫ ማዕከላትንና 6 ትምህርት ቤቶችን በአጠቃላይ 55 የሚሆኑ የመሰረተ ልማት መገልገያ ፕሮጀክቶች መሟላታቸው ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል ቦርዱ፥ ፕሮጀክቱ በቅርቡ በሶማሌ ክልል አንዳንድ አከባቢዎች ላይ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ለመቋቋም ያደረገውን አስተዋጽኦና በቀጣይም ሊከሰቱ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቋቋም የነደፈውን እቅድ መገምገሙን ከሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የቆላማ አከባቢና ተፋሰስ ልማት ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢብራሂም ዑስማን÷ በፕሮጀክቱ  የሥራ አፈጻጸምና ዕቅድ ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለማረም፣ የፕሮጀክቱ አስተዳደር አካላት እቅዱ ላይ መካተት ያለባቸው ምክረ ሀሳቦችንና በግብዓትነት መወሰድ ያለባቸው እንዲሁም ጥንካሬዎችን ማጠናከር በሚቻልበት ላይ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.