Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል አዲስ የመንግስት ምስረታ የፊታችን ሰኞ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ እና የመንግስት ምስረታ የፊታችን ሰኞ ይካሄዳል፡፡
 
የሶማሌ ክልል መንግስት ምክር ቤት በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለክልል ምክር ቤት አሸናፊ ለሆኑ አዳዲስ የምክር ቤት አባላት በዛሬው ዕለት ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡
 
ስልጠናው በምክርቤቱ ስነ -ምግባርና ህግ፣ በምክር ቤት አባላት መብትና ግዴታ እንዲሁም ስለ ምክር ቤቱ የስራ አደረጃጀት እና አጠቃላይ መሰረታዊ መርሆች ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
 
የሶማሌ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሐላፊ ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ÷ 90 በመቶ አዲስ የሆነው የምክር ቤት አባል በባለፉት ጊዜያት የክልሉ መንግስት በተለያዩ ተቋማት ላይ ስኬታማ የለውጥ መዋቅር ስራዎች እንደሰራው ሁሉ በምክር ቤቱ አሰራር ላይም የማሻሻያ ስራዎች እንደሚጠበቁ አንስተዋል፡፡
 
ሁሉም የምክር ቤት አባል ካለፉት ዓመታት የበለጠ ህዝቡ የተሻለ ስራና አገልግሎት እንደ ሚጠብቅ መረዳት እና ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
 
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ መለው ኢብራሂም በበኩላቸው÷ የምክር ቤቱን ህግና ደንብ ፣ መብትና ግዴታ እንዲሁም አጠቃላይ ድንጋጌና አሰራርን ማወቅ ጠቃሚና መሰረታዊ በመሆኑ አባላቱ በትኩረት ሊከታተሉት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
 
የክልሉ ምክር ቤት ስድስተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ እና የመንግስት ምስረታም የፊታችን ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚካሄድ መገለጹን የሶማሌ መገናኛ ብዙሓን ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.