Fana: At a Speed of Life!

የሸገር ዳቦ በተመጣጣኝ ዋጋ በ400 ማከፋፈያዎች እየተሰራጨ እንደሚገኝ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሸገር ዳቦ በተመጣጣኝ ዋጋ በ400 ማከፋፈያዎች ለአዲስ አበባና አካባቢው ነዋሪዎች እየተሰራጨ እንደሚገኝ ተገለፀ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሲሳይ ደበበ እንደገለፁት፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ የሚያመርታቸውን ዳቦዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪዎች ማሰራጨት ጀምሯል።

ፋብሪካው በዋነኛነት የዳቦ ዋጋን የህብረተሰቡን ገቢ ግንዛቤ ያስገባ እና አነስተኛ ዋጋ የማቅረብ አላማን ይዞ እንደመግባቱ ተደራሽነቱ ላይ በጥብቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በተለይም በግብይት ሂደቱ ሰንሰለቱን በማሳጠር በመሀል የሚገባ ደላላን ለመከላከል በራሱ ተሽከርካሪዎች እያከፋፈለ ይገኛል ነው ያሉት ኢንጂነር ሲሳይ ደበበ ።

በፋብሪካው የተመረተው ዳቦ በከተማዋ ለህብረተሰቡ ተደራሽ በሆኑ በተመረጡ ቦታዎች በከተማ አስተዳደሩ በተደራጁ ወጣቶች አማካሽኝነት አቅርቦቱ ቀጥሏል ነው ያሉት ።

የሸገር ዳቦ አሁን ላይ በቀን 600 መቶ ሺህ ዳቦ እያመረተ ለአዲስ አበባና አካባቢው ነዋሪዎች እያሰራጨ ሲሆን፥ በቀጣይም በሙሉ አቅሙ ለማምረት እቅድ ስለመያዙ ገልጸዋል ።

የሸገር ዳቦ ፋብሪካ በቀጣይ እስከ 2 ሚሊየን ዳቦ በቀን የማምረት አቅሙን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑም ይታወቃል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባውና በሰዓት 80 ሺህ፤ በቀን እስከ 2 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርተው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ባሳለፍነው ሰኔ 18 2012 ዓ.ም በይፋ መመረቁ ይታወሳል።

በሀይለኢየሱስ መኮንን

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.