Fana: At a Speed of Life!

የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት የገነባው የልዩ ፍላጎት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት የገነባው የልዩ ፍላጎት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ።

ለገጣፎ በሚገኘው ዲቦራ ፋውንዴሽን ጊቢ ውስጥ በ19 ሚሊየን ብር የተገነባው የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤትን ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው መርቀዋል።

ትምህርት ቤቱ የአይምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ታዳጊዎች አገልግሎት የሚሰጥ ነው ፡፡

ፅህፈት ቤቱ ያስገነባው የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት በሀገራችን የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ታዳጊዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እጥረትን በተወሰነ ደረጃ እንደሚቀርፍ ተመልክቷል።

ፕሮጀክቱ በውስጡ ስምንት ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች አመቺ የሆኑ ክፍሎችና ሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ክፍሎችን የያዘ ነው።

የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት እስካሁን ይህንን የልዩ ፍላጎት ጨምሮ 24 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ገንብቷል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ፥ ወላጆች የአእምሮ ውስንነት ያላቸውን ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩና አቅም ያላቸው አካላት ደግሞ በዚህ አይነት በጎ አላማ የተሰማሩ ድርጅቶችን እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከፅህፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.