Fana: At a Speed of Life!

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዲጂታል ጤና ፈጠራ መማሪያና መረጃ ማዕከል ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዲጂታል ጤና ፈጠራ መማሪያና መረጃ ማዕከል ተመረቀ።

የጤና ፈጠራና መማሪያና መረጃ (የኢኖቬሽን) ማዕከሉንም በዛሬው ዕለት የጤና ሚኒስቴር ዶክተር ሊያ ታደሰ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ መርቀው ከፍተዋል።

በምርቃቱ ወቅትም የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ፥ መረጃ ላይ የተመሰረተ የውሳኔ አሰጣጥ ልምድን ማዳበር በጤና ባለሙያው ላይ የሚሰራ መረጃን ሰብስቦና ተንትኖ የመጠቀም አቅም ማጎልበትና በጤና መረጃ ዋጋ መስጠት ላይ ባለ አተያይ ዙሪያ የባህሪ ለውጥ ማምጣትን መሰረት አድርጎ ከፍተኛ ስራዎችን ማከናወን እንዲሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የመረጃ አሰባሰብ፣ አያያዝ፣ አተናተንና አጠቃቀም ሂደቱን ዘመኑ በሚጠይቀው አግባብ በቴክኖሎጂ በማዘመን ቀላልና ወጪ ቆጣቢ ማድረግ ላይ እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቅዋል።

የኢኖቬሽን ማዕከሉ መከፈቱ በጤናው ዘርፍ የመረጃ አብዮትን ለማምጣት የተያዙ ዕቅዶችን ለመተግበር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ማዕከሉ በተለይም በጤናው ሴክተር ውስጥ ለምተው የሚተገበሩ ሶፍቴዌሮች የተጠቃሚውን ፍላጎት መሰረት አድርገው እንዲለሙ የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል።

እንዲሁም በለማው ማስተግበሪያ ዙሪያ በዘላቂነት ለመተግበርና ለመደገፍ እንዲቻል በቂ አቅም እንዲፈጠርና የመንግሰት ባለቤትነት እንዲረጋገጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት መሆኑና ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ የስልጠናና የስራ ላይ ልምድ ዕድሎችን በመፍጠር በሙያው የሰለጠኑ ወጣቶችን ተሳትፎ ለመጨመር እንደሚረዳም ዶክተር ሊያ አስረድተዋል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ታምሩ አሰፋ በበኩላቸው፥ ከዛሬ 57 ዓመት በፊት በአፄ ኃይለስላሴ ለቲቢ ህሙማን መታከሚያ ቤት ብለው በከፈቱት በውቅቱ ጀግና አርበኛ የነበሩት የራስ አበበ አረጋይ መኖሪያ ቤት የነበረው ህንጻ ታድሶ ማዕከሉ መገንባቱን አስታውቀዋል።

ለቲቢ ህሙማን ህክምና ማገገሚያ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ሆስፒታሉ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ አገልግሎቱን በማሳደግ በአሁኑ ሰዓት 35 የሚሆኑ የህክምና አገልግሎቶችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሆስፒታሉ የመረጃ አያያዝን ለማዘመን በኮምፒውተር የታገዘ የህክምና መረጃ አያያዝ ስርዓት ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም መናገራቸውንም ከቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ማዕከሉ በጤና ሚኒስቴር፣ በቢልና ሚሊንዳ ፋውንዴሽን እና በሆስፒታሉ ትብብር የተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

ለማዕከሉ መመስረት ትልቅ አስተዋጽኦ ላደረጉት የቢልና ሜሊንዳ ፈውንዴሽን የአፍሪካ የጤና ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሰሎሞን ዘውዱ የምስጋና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.