Fana: At a Speed of Life!

የበረሃው አንበጣ ዳግም በመንጋ ደረጃ እንዳይከሰት ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ – ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ የበረሃው አንበጣ መንጋ ዳግም በመንጋ ደረጃ እንዳይከሰት ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ ገለጹ፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፦ የአንበጣው መንጋ በቀጣይ እንዳይከሰት ዕንቁላል የጣለበትን ቦታ የመለየት ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

ይህንንም ለመከላከል ዘጠኝ ሄሊኮፕተሮች መኖራቸውንም ነው የጠቀሱት፡፡

እንዲሁም 116 ተሸከርካሪዎች መዘጋጀታቸውንም ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሁለት ሄሊኮፕተሮች መጋጨታቸውንና ሁለቱ ደግሞ ለጥገና ወደ ውጭ በመላካቸው መከላከሉ ላይ ተጽዕኖ አሳድረው እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

አሁን በተጠናከረ ሁኔታ በአፋር፣ በሶማሌና በአዋሳኝ ክልሎች ላይ የመከላከል ስራ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

አያይዘውም በአሁኑ ወቅት የማጽዳት ስራ እንጂ አሁን ላይ አንበጣ በመንጋ ደረጃ የለም ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮችም አንበጣ መከሰቱን ሪፖርት ካደረጉ ጥቆማውን በመከተል ርጭት እንደሚካሄድ አንስተዋል።

እንዲሁም በሃገር አቀፍ ደረጃ የኬሚካል እጥረት እንደሌለ ገልጸው 137 ሺህ ሊትር መኖሩን ነው የጠቀሱት፡፡

ከዚህ ባለፍም አሁን ላይ 50 ሺህ ሊትር ደግሞ ከውጭ እየገባ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው ኬሚካል በግለሰብ ደረጃ እንደማይሰጥ የጠቀሱ ሲሆን ይህ የሚሆነው ኬሚካሉ በርጭት ወቅት በሰዎች ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ ለጥንቃቄ ታስቦ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

ጉዳት እንዳያደርስም የኬሚካል መከላከያ ልብሶችን ለሚያጠልቁ ስካውቶች እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.