Fana: At a Speed of Life!

‘የበቃ’ ንቅናቄ ሰልፍ በስዊድን ከተሞች ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘የበቃ’ ንቅናቄ አካል የሆነው ሰላማዊ ሰልፍ በስዊድን ስድስት ከተሞች ተካሄዷል።

በተመሳሳይ የዘመቻው አካል የሆነ ሰልፍ በኖርዌይ መዲና ኦስሎ ተከናውኗል።

የስዊድን ስቶኮሆልም ሰልፍ መነሻውን ‘ስቱሬጋታን’ ከተሰኘ አካባቢ መድረሻውን ‘ኖራ ባንቶርጌት’ እየተባለ በሚጠራው አደባባይ በማድረግ ተካሄዷል።

በሰልፉ ላይ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች መሳተፋቸውን በስዊዲን የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባል ወይዘሮ የሺ ወንድሜነህ ገልጸዋል።

ሰልፎቹ የምዕራቡ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት እንዲሁም አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች የፈጸማቸውን አሰቃቂ ድርጊቶች የሚያወግዙ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የሰልፉ ተሳታፊዎች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪዎቹን ህወሓትና ሸኔ ቡድኖች ማውገዝ እንደሚገባቸውና ከኢትዮጵያ እውነት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል።

‘የበቃ’ ንቅናቄ አካል የሆነው ሰላማዊ ሰልፍ በስቶኮልም፣ ጉተንበርግ፣ ሉንድና ሌሎች ሶስት የስዊድን ከተሞች ላይ መካሄዳቸውንም ነው ወይዘሮ የሺ የገለጹት።

በስዊድን ከተሞች የተካሄደውን ሰልፍ ያዘጋጁት በስዊድን የሚኖሩ የኢትዮጵያና ኤርትራ ኮምዩኒቲ አባላት እንደሆኑ ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና ‘የበቃ’ ዘመቻ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በኖርዌይ መዲና ኦስሎ ተካሄዷል።
ሰልፉ መነሻውን ኦስሎ ‘ሴንትራል ስቴሽን’ መዳረሻውን በኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማድረግ መካሄዱን ከሰልፉ አስተባባሪዎች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በሰልፉ ‘አሜሪካና ምዕራባውያን አገራት እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ያንሱ’ ፤ ‘ኢትዮጵያ ታሸንፋለች’ እና ሌሎች ‘የበቃ’ እንቅስቃሴ መልዕክቶች መተላለፋቸው ተገልጿል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳትፈዋል።

‘የበቃ’ ንቅናቄ አካል የሆኑ ሰላማዊ ሰልፎች ነገ በአውስትራሊያ ሜልቦርንና ቪክቶሪያ፣ በግሪክ አቴንስና በዴንማርክ ኮፐንሄገን እንደሚካሄዱ ኢዜአ ከዘመቻው አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ በኡጋንዳ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች “ከእናት ሀገሬ ኢትዮጵያ የሚበልጥብኝ ማንም የለም” በሚል የበቃ እንቅስቃሴ አካል የሆነውን መርሃ ግብር ዛሬ በካምፓላ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ቅጥር ጊቢ አካሂደዋል።

በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ኡጋንዳዊው ፓንአፍሪካኒስት እና የህግ ባለሙያ ሚስተር ቱሃሚ ሮድኔይ ÷ “እኛ አፍሪካውያን የራሳችንን ችግር ለመፍታት አፍሪካዊ መፍትሄ አለን የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነትን በቃ ማለት አለብን ፤ የኢትዮጵያውያንን ትግል ተቀላቅለናል” ብሏል።

በኡጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለምጸሀይ መሰረት ÷ ኢትዮጵያ በአሸባሪው ህወሓት እና በውጪ ሀይሎች የተከፈተባትን ጦርነት እየመከተች እንደምትገኝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.