Fana: At a Speed of Life!

የበየነመረብ ስነ-ምግባር- በዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)
የበይነመረብ ስነ-ምግባርን በተመለከተ ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ ከጀርመን በርሊን ሀሳብ አጋርተውናል ፤ ስለፍቃደኝነታቸው እና በዚሁ ጉዳይ ላይ ሀሳባችውን በጽሁፍ ስላጋሩን ከልብ እናመሰግናለን፡፡
ዶክተር ፀጋዬ ሙያዊ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አቅርበዋል፡-
በቅድሚያ የበይነ መረብ እና ማህበራዊ ትስስሮች ኮሚዩኒኬሽን ስነምግባር በተመለከተ አስተያየቴን እንድሰጥ በመጠየቁ አመሰግናለሁ።
ርዕሰ ጉዳዩ ሰፊ ስለሆነ በአጭሩ ለመግለጽ ከባድ ቢሆንም እንደሚከተለው አስተያየቴን አቀርባለሁ። በዘመነ ዲጄታል ሰው ከማህበራዊ ኢንጅነሪንግ ተነስቶ ዛሬ ምሁራዊ የዲጅታል ሀብትን በመጠቀም የሰው ልጅ የተሸለ እንዲኖር ማህራዊ ተጽእኖ የሚፍጠር የማህበራዊ ቴክኖሎጂ ላይ ደርሷል።
ይህ ዲጄታላዊ የመቀየር ሥርዓት ጥሩ ነገርን እንዳመጣ ሁሉ ጎጂ ሁኔታም ተከስቷል። ለምሳሌ የማንነት ስርቆት፣ መረጃዎችን መጥለፍ፣ ማጭበርበር፣ ሞቢንግ፣ ማስፈራራት፣ የሀሰት ዜና፣ ስም ማጥፋት፣ ማጋጨት… ወዘተ. የመሳሰሉት በኋላ የተፈጠሩ ናቸው።
የበይነመረብ ስነምግባር በመባል የሚታወቀው በአጠቃላይ የሚመክረን ሰው አክባሪ መሆንን፣ አስተያየቶቻችን እንዴት ሊነበቡ፣ ሊገነዘቡ ወይም ሊተረጎሙ እንድሚችሉ መረዳት ለምሳሌ እኔ ስለኮሮና ልምድ ስጽፍ ከመልቀቄ በፊት ሌላ አስነብቤ እና አስተያየት ጠይቄ መሆን ይኖርበታል፣ የሚጻፈውን የሚጋሩት ማን እንደሆኑ እና እነሱም መልሰው ለማን እንደሚያጋሩት መገመት፣ በአንድ ቡድን ውስጥ ወይም የማህበራዊ ትስስር የጓደኛ ጥያቄዎችን እና የቡድን ጥሪዎችን ከመቀበላቸው በፊት መፈተሽ፣ “ይህንን ለተወሰነ ቁጥር አስተላልፍ” የሚል Hoax መልእክቶችን አለማስተላለፍ፣ የስነምግባር ደንቦችን መጠየቅ፣ ስህተትን ማውቅ እና ከተደረገም ይቅርታ መጠየቅ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡
የኢንተርኔት ስነ-ምግባርን መጣስና ወደወንጀል ለመተላለፍ ቀዩ መስመር በጣም የሳሳ ነው። ይህንንም ብዙ ሰው በደመ-ነፍስ ሲፈጽመው ይታያል። ብዙ ሰዎች ያለፈቃድ አንድን ሙዚቃ በመገልበጥ፣ አንድን ሶፍትዌር፣ ሙዚቃ፣ ፊልምን ፍቃድ ከሌለው ሰው ገዝቶ በመጫንና የአእምሮ ንብረት ስርቆት በመፈፀም ከዚህ ይጀምራሉ። ስለሰዎች በመናገር፣ በስሜት አስተያየት በመስጠት ወይም ይህንን በመጋራት ወዘተ ሳይታወቅ ህግ እና ደንቦችን ይጣሳሉ።
የጀርመን የኔትወርክ ኢንፎርሰመንት ህግ በተለምዶ የፌስ ቡክ ህግ (NetzDG) የሚባለው በማህበራዊ ሜዲያ ላይ የሚቀርቡትን የጥላቻ ንግግሮችን፣ የሀሰት ዜናዎችን እና የሳይበር ወንጀሎችን የሚቆጣጠር ሲሆን፣ ወንጀሉን ፈጻሚው ግለሰብ ወይም ቡድን ብቻ ሳይሆን አቅራቢውንም የሚጠይቅ ነው። በዚህም የሚዲያ ፕላት ፎርሞች በየሶስት ወሩ መረጃ እንዲያቀርቡ ይጠበቅባቸዋል።
ለምሳሌ በኢንተርኔት ላይ ወይም በማህበራዊ ትስስር መድረኮች የአንድ ሰው ስም ከተጠቀሰ ይህ የሰውን የስም መብት እና ክብርን መጎዳት ሊሆን ይችላል የተጠቀሰው ነገር እንኳን እውነት ቢሆን።
በጀርመን ወንጀል ህግ እንደ ስድብ (§ 185 StGB)፣ ስም ማጥፋት (§ 186 StGB) ከሚታዩበት በተጨማሪም ግለሰባዊ መርጃን ያለግለሰቡ ፈቃድ መግለጽ የሳይበር ህግ እና የዳታ መከላከል ህግ (Datenschutz-Grundverordnung: DSGVO) ሊያስጠይቅም ይችላል።
ሌላው ነገር ግን በበይነመረብ መድረኮች ወይም በሌሎች በኢንተርኔት መድረኮች ላይ የሰዎች ስም ሳይጠቀስም እንዲሁ የስም ወይም የግል መብትን በመጣስ ሊያስቀጣ ይችላል። ይህ ድብቅ ስም ማጥፋት የሚባለው ነው።
ይህ የሚሆነው የሰው ክብርን የሚያወርድ ወይም የሰውየውን ጥፋተኛነትን በሚገልጹ መልኩ ሆኖ ግን አንባቢዎቹ ያለስም የተጠቀሰውን ሰው ማን እንደሆነ መመደብ የሚያስችሉ የተደበቁ መግለጫዎች ጋር ሲቀርብ ነው። ለምሳሌ የሚያገናኙ ቦታዎችን፣ ድርጊቶችን፣ ማንነቶችን፣ አመልካክቶችን ከዚህ በፊት ከተፍጠሩ ኩነቶች ጋር አንባቢ አገናዝቦ ስለማን እንደሆነ እንዲረዳ ሆኖ ሲቀርብ ነው።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ ገብተን ስንወጣ ዱካችንን ጥለን ነው የምንወጣው። ለምሳሌ የጻፍነውን እንኳን ብንሰርዘው ይህ ከአቅራቢው ሰርቨር ላይ እንደተከማቸ ይቀራል። በዳታ ማይኒንግ እና ሌሎች የዲጂታል ዳሰሳ ቴክኖሎጂዎች እኛን በይበልጥ ለማውቅ ይረዳቸዋል።
እንደነ ኢመዞን፣ ኢቤይ የመሳሰሉት ኩባንያዎች እንኳን አሁን ያዘዝነውን ቀርቶ ለወደፊቱም የምናዘውንም አስቀድሞ የማወቅ ብቃት ላይ እየደርሱ ማንነታችን ፕሮፋይል በማድረግ በአጠቃላይ እንቅስቃሴያችን በጥቂት ሰአታት ማስቀመጥ የሚችሉበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው።
የፌስቡክ እና ትዊተር አካውንቶችን ለመክፈት መስፈርቱ እውነትኛ ስም/ እውነትኛ ማንነት/የትውልድ ቀን በመስጠት እና ውሎች እና ፖሊሲዎችን (termns and policies) በማረጋገጥ የሚከፈት ሲሆን ከዚህ የሚጻረር የተሳሳተ መርጃ መስጠት በእነዚህ ሶሻል ሚዲያዎች መጠቀምን ያሳግዳል። አብዛኛው የጥላቻ ንግግር እና የሃሰት ዜና የሚያስተላለፉት ሰዎች የቅጽል ስም ወይም የፈጠራ ስም በመጠቀም ነው። ይህም የፌስቡክ እና ትዊተርን የመጠቀም ደንብ የሚጻረር ሲሆን የሚያሳግድም ነው።
ቢሆንም የIP አድራሻችውን፣ የኮምፒውተር ወይም የስማራትፎን መርጃቸውን ሳያውቁት አስመዝግበው ስለሚገቡ ለማግኝት ብዙም አያዳግትም።
አብዛኛው ለአገራችን በማሰብም ወይም በመቆጨትም ሊሆን ይችላል በስሜት የምንጽፋቸው ጽሁፎችን ከማጋራታችን በፊት ለቅርብ ገለልተኛ ጓደኛ ልኮ ማማከር፣ ወደ ቡድን የሚላክ የድምጽ መልእክት ካለም በተቻለ መጠን ማሳጠር፣ ነገሮችን እና ሰዎችን ነጣጥሎ ማየት፣ የተላለፉ መርጃዎችን “ነው” ከማለት ይልቅ “እንደደርሰኝ”፣ “እንደሚታየው“ ብሎ መግለጽ ይመረጣል። መልካም ማሰብ እና ማበረታታት ወሳኝ ውጤት አለው። (ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ)
በስላባት ማናዬ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.