Fana: At a Speed of Life!

የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችና አሰባሳቢዎች ማህበር ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ የተመሰረተው ማህበሩ ከ200 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በመያዝ ነው።
የኢትዮጵያ ደም ለጋሾች ማህበር ፕሬዚደንት አቶ ብዙአየው ጌታቸው የማህበሩ ምስረታ ዋና አላማ በተለያዩ ወቅቶች የሚከሰተውን የደም እጥረት ችግር ለመፍታት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ማህበሩ ህብረተሰቡ ደም የመለገስ ልምዱ እንዲዳብር ለማስቻል የተለያዩ ኩነቶችን በማዘጋጀት ይሰራል ብለዋል።
በመዲናዋ የሚንቀሳቀሱ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የደም ለጋሾች ማህበር አባል እንዲሆኑ የማህበሩ አባላት እንደሚሰሩም አቶ ብዙአየው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በድሬዳዋና ሌሎች የክልል ከተሞች የማህበሩን እንቅስቃሴ በማስፋት የደም ልገሳ ባህል እንዲዳበር ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ያረጋል በንቴ÷ በኢትዮጵያ የደም አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል ብዙ መስራት ይገባል ብለዋል።
ለዚህም የደም ልገሳ ማህበራት ምስረታ እውን መሆን ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በተለያዩ ክልሎች ያሉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የደም ልገሳ በማድረግ እጥረቱን ለመፍታት በርካታ ጥረቶች ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው÷ ይሄው በጎ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከ21 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ለማሰባሰብ እቅድ መያዙን ጠቅሰው÷ ለዚህም ክበባትን በማጠናከር የወጣቶችን ተሳትፎ ማጎልበትና በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን ማብዛት ይገባል ብለዋል።
ከማህበሩ መስራቾች ወጣቶችም ቀደም ሲል የደም ልገሳ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው በቀጣይም የበጎ ፈቃድ አገልግሎታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ማህበሩ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በመንቀሳቀስ የደም ልገሳ በማከናወን እንዲሁም ደም ለጋሾች እንዲበራከቱ ቅስቀሳ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.