Fana: At a Speed of Life!

የቡድን 20 አባል ሀገራት ለስድስት ወራት የሚቆይ የእዳ መክፈያ የእፎይታ ጊዜ ለመስጠት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቡድን 20 አባል ሃገራት ለታዳጊ ሀገራት ለስድስት ወራት የሚቆይ የእዳ መክፈያ የእፎይታ ጊዜ ለመስጠት መስማማታቸውን አስታወቁ።
የቡድን 20 አባል ሀገራት የእፎይታ ጊዜውን ለመስጠት የተስማሙት በኮቪድ 19 ምክንያት ኢኮኖሚያቸው ክፉኛ የተጎዱ ሀገራትን ለመደገፍ በማሰብ መሆኑን ገልጸዋል።
የእፎይታ ጊዜው እስከሚቀጥለው ዓመት የፈረንጆቹ ሰኔ 2021 ድረስ ይቆያል ተብሏል።
እፎይታው ታዳጊ ሀገራትን የጤና ዘርፋቸውንና ኢኮኖሚያቸውን ለማነቃቃት ይረዳቸዋል ነው የተባለው።
በአንጻሩ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች በጊዜው ማጠር ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የዕርዳታ ድርጅቶቹ ታዳጊ ሀገራት አሁንም ቢሆን ለህይወት አድን ስራ ከሚያወጡት በላይ ዕዳ እየከፈሉ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኦክስፋም ባለሥልጣን ጃሜ አቴንዛ በበኩላቸው የታዳጊ ሀገራትን እዳ ያለመሰረዝ በሀገራቱ ላይ ያለውን ዕዳ ያበዛል ብለዋል።
እንዲሁም በጤና ዘርፉ እና በማህበራዊ ግልጋሎት ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዳያፈሱ ያደርጋል ሲሉም ተደምጠዋል።
የቡድን 20 አባል ሀገራት የግል አበዳሪዎችም የእፎይታ ጊዜው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፡-አልጀዚራ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.