Fana: At a Speed of Life!

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር  ዶክተር ሂሩት ካሰው በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ የሚገኘውን ብሔራዊ ስታዲየም ጎበኙ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር  ዶክተር ሂሩት ካሰውን  ጨምሮ ከፍተኛ የስፖርት አመራሮች በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ የሚገኘውን ብሔራዊ ስታዲየም ጎብኝተዋል ፡፡

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ አካባቢ በቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ስራ ተቋራጭነት በኤም ኤች ኢንጅነሪንግ አማካሪነት እየተገነባ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተገነባ ይገኛል ፡፡

የግንባታ ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሰው ፣ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር  አቶ ኤሊያስ ሽኩር እና ሌሎች አመራሮች በቦታው በመገኘት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል ፡፡

በጉብኝታቸው ወቅትም የግንባታ ተቋራጭ ድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ሚስተር የን ስለግንባታው ለአመራሮቹ ገለፃ አድርጓል፡

በገለፃውም ከግንባታ እቅድ ጀምሮ የግንባታ ቁሳቁስ አቅርቦት እና የሰው ሀይል ስምሪት እንዲሁም በግንባታ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን ለአመራሮቹ አቅርቧል ፡፡

ተቋራጭ ድርጅቱ ለስታዲየሙ ግንባታ አገልግሎት የሚውሉ ቴክኖሎጅዎችን እና ቁሳቁሶችን ለማስገባት የምንዛሪ እጥረት እንደገጠመው ገልጿል ፡፡

በተጨማሪም በሳይት ፕላኑ ላይ በህገ ወጥ መልኩ የተሰሩ ቤቶች አለመነሳታቸው ግንባታውን በተያዘለት ፍጥነት ለማካሄድ እንቅፋት እንደሆነበትም አንስቷል ፡፡

የግንባታ ጥራት ተቆጣጣሪ እና አማካሪ ድርጅት በበኩሉ ÷ፕሮጀክቱን የሚመጥን ፕሮፌሽናል ባለሙያዎችን ከማሰማራት እና ወጥ የሆነ እቅድ አውጥቶ ወደ ስራ ከመግባት አኳያ ተቋራጭ ድርጅቱ ክፍተቶች እንዳሉበት አውቆ ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጿል ፡፡

ዶክተር ሂሩት ከጉብኝቱ በኃላ በሰጡት አስተያየት ÷ውል በተገባው መሠረት የስታዲየሙ የማጠቃለያ ስራዎች የተጀመሩ ቢሆንም በሚፈለገው ፍጥነት ግን እየሄደ እንዳልሆነ ገልፀዋል ፡፡

በመሆኑም በአንድ ሳምንት ውስጥ አማካሪ ድርጅቱ እና ተቋራጭ ድርጅቱ የጋራ መግባባት የተደረሰበት እቅድ በማውጣት ግንባታው ሊፋጠን እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡

ተቋራጭ ድርጅቱ ግንባታውን በጥራት እና በፍጥነት ማካሄድ የሚያስችል የሰው ሀይል ስምሪት ሊያደርግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ፡፡

በሌላ በኩል በሳይቱ ላይ የሚገኙትን ህገ ወጥ ሰፋሪዎች ለማስነሳት የተጀመረ ጉዳይ መኖሩን ጠቁመው÷ በቀጣይም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን እልባት እንደሚያገኝ ተናግረዋል ፡፡

የምንዛሪ እጥረትን በመለከተ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ ይሞከራል ብለዋል ፡፡

የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነርአቶ ኤሊያስ ሽኩር በበኩላቸው÷ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እና ጥራት እንዲጠናቀቅ ኮሚሽኑ እቅድ አውጥቶ ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

አጠቃላይ ፕሮጀክቱም 48 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን÷ከ62 ሺህ በላይ ተመልካች የመያዝ አቅም አለው ተብሏል።

ስታዲየሙን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ከ 8 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ይሆናልም ነው የተባለው።

በሁለተኛው እና የማጠቃለያ ምዕራፍ ግንባታ የመጫወቻ ሜዳውን ሳር ማልበስ፣ የመሮጫ ትራክ ማንጠፍ፣ የስታዲየሙን ጣሪያ ማልበስና ወንበር መግጠም ፣ሰው ሰራሽ ሀይቅ፣ የሄሊፕተር ማረፊያ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ ፣ ሳውንድ ሲስተም ፣ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች፣ የመለማመጃ ሜዳዎች እና ሌሎች የማጠቃለያ ስራዎች እንደሚያካትት ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.