Fana: At a Speed of Life!

የባቫሪያን ራስ ገዝ አስተዳደር ኮቪድ19ን ለመከላከል ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ከባቫሪያን ራስ ገዝ አስተዳደር የአውሮፓ ጉዳዮችና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ሚላኔ ሁመል እና በኢትዮጵያ ከጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አውር ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ ኮቪድን በመከላከል እና በመቆጣጠር ዙሪያ ከጅምሩ አንስቶ በርካታ ጥረት ስታደርግ መቆየቷንና የጀርመን መንግስት ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በሙኒክ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እና በጅማ ዩኒቨርሲቲ በኮቪድ19 የበሽታ መከላከል አቅም ጥናት ፕሮጀክት እንዲሁም በተግባረእድ ፖሊ ቴክኒክና በሙኒክ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ በጋራ እየተሰራ ባለው የኮቪድ19 መከላከል ፌስ ማስክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት እየተደረገ ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አያይዘውም በኢትዮጵያ የኮቪድ19 መከላከያ ክትባትን ለዜጎች በማዳረስ የትብብር ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡

የባቫሪያን ራስ ገዝ አስተዳደር የአውሮፓ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ሜላኔ ሁምል በበኩላቸው፥ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ የጤና ስራዎች፣ በትምህርት ፣ በግብርና ፣ በሰው ሀይል ልማት የረጅም ጊዜ ትብብር እንደነበራት አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ኮቪድ19 ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እያደረገች ያለውን ጥረት ለማገዝ የተጀመሩ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አውር፥ የግማሽ ሚሊየን የአፍና የአፍንጫ መከለያ ማስኮችን ድጋፍ ለጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስረክበዋል፡፡

አምባሳደሩ የተጀመሩ የትብብር ስራዎች በተለይም የኮቪድ19 መካላከል፣ የሃገር ውስጥ የህክምና ምርቶችን ማጠናከር እና የጤና እውቀት ሽግግር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት የፕሮጀክቶቹ የጥናት ሂደቶች በሁለቱም ሀገራት የትምህርት ተቋማት ቀርበው ወይይት እንደተካሄደባቸው የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.