Fana: At a Speed of Life!

የባንክ አገልግሎትን በሂደት ለዓለም አቀፍ ውድድር ክፍት በማድረግ ባንኮች አቅማቸውን እያጎለበቱ እንዲሄዱ መስራት ይገባል -አቶ አቤ ሳኖ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአገር ውስጥ የባንክ አገልግሎትን ቀስ በቀስ ለዓለም አቀፍ ውድድር ክፍት በማድረግ ባንኮች አቅማቸውን እያጎለበቱ እንዲሄዱ መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ተናገሩ።
 
የአገር ውስጥ ባንኮች ከአቅም በላይ በሆነ ውድድር ከገበያ ውጭ እንዳይሆኑ ለማድረግ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ለዓለም ገበያ ዝግ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።
 
አቶ አቤ ሳኖ የባንክ አገልግሎትን ዘርፍ ለዓለም ገበያ ዝግ በማድረግ የአገር ውስጥ ባንኮችን አቅም መገንባት እንደማይቻል ተናግረዋል።
 
የባንክ አገልግሎቱን እንደተዘጋ ማቆየት የአገር ውስጥ ባንኮችን እድገት እንደሚያቀጭጨው ጠቁመው÷ በተቃራኒው የባንክ አገልግሎቱን ድንገት ለዓለም ገበያ ወለል አድርጎ መክፈትም የአገር ውስጥ ባንኮች እንዲዋጡ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
 
በመሆኑም የባንክ አገልግሎቱን ቀስ በቀስ ለዓለም አቀፍ ውድድር ክፍት በማድረግ የአገር ውስጥ ባንኮች የውድድር አቅማቸውን እያጎለበቱ እንዲሄዱ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
 
የባንኮች አቅም የሚገነባው ገበያውን በመዝጋት ሳይሆን በልካቸው የሚወዳደሩበትን አሰራር በመዘርጋት መሆኑንም ጠቁመዋል።
 
በተወሰነ የአክሲዮን ድርሻ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በማድረግ በሂደት የአክሲዮን መጠናቸውን እያሳደጉ የሚሄዱበትን አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ አመላክተዋል።
 
ይህን ማድረግ የአገር ውስጥ ባንኮችን ባጠረ ጊዜ ወደተሻለ ብርታት ሊያመጣቸው እንደሚችል ማብራራታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.