Fana: At a Speed of Life!

የብሄራዊ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በትውልድ መካከል ኢትዮጵያዊ በጎነት መተሳሰብና መከባበር እንዲጠነክር የሚያስችል ነው- ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሄራዊ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በትውልድ መካከል ኢትዮጵያዊ በጎነት መተሳሰብና መከባበር እንዲጠነክር የሚያስችል ታሪካዊ ተግባር መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለፁ።
ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በዛሬው እለት የተጀመረውን የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠናን አስመክልተው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም፥ “ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያችን ምሰሶ የነገ ተስፋችን ነፀብራቅ ነው፤ ከወጣት ጉልበት ውስጥ ሃገር ትወለዳለች፤ ከብሩህ የወጣት አእምሮ ውስጥ አዳዲስ ሃሳቦችና የሃገር ትልሞች ይነደፋሉ፤ መግባባቶችና አብሮነቶች ይመነጫሉ” ብለዋል።
የብሄራዊ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በትውልድ መሃከል ኢትዮጵያዊ በጎነት መተሳሰብና መከባበር እንዲጠነክር፤ ብሄራዊ መግባባት እና አገራዊ ፍቅር እንዲጎለብት የዘላቂ ኢትዮጵያዊ ሰላም ሚስጥርም ጎልቶ እንዲወጣ የሚያስችል ታሪካዊ ተግባር ነው” ሲሉም ገልፀዋል።
በዚህ እንቅስቃሴ ወጣቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ፣ በአካባቢው ጉዳይ፣ በማህበረሰቡ ጉዳይ ላይ በነፃነት እንዲወያይ እንዲከራከር የራሱን ዘመን በዘመኑ ተሻጋሪ ሃሳቦች እንዲመራ እድል የሚሰጥ መሆኑንም አስታውቀዋል።
“እኛን ምሰል፤ እኛ የምናስበውን በግድ አስብ ከሚል ኋላ ቀር አስተሳሰብ ተሻግሮ ነፃ በሆነ መንገድ በመረጠው አጀንዳ ላይ ይወያያል ሃሳቡንም ይቀያየራል” ብለዋል።
በዚህም መሰረት “ዛሬ የመጀመርያ ዙር የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠናን በ11 ዩኒቨርስቲዎች በይፋ አስጀምረናል” ሲሉም ገልፀዋል።
በአጭር ቀናት ውስጥ ደግሞ ተጨማሪ 11 ዩንቨርሲቲዎች ተካተው በ22 ዩንቨርሲቲዎች 35 ሺህ ከዩንቨርሲቲ ተመራቂ ወጣቶች ስልጠና ለተከታታይ 45 ቀናት እንደሚወስዱም አስታውቅዋል።
በስልጠናው ለቀጣይ ህይወታቸው የሚጠቅማቸው በስሜታዊ ብስለት፣ አእምሯዊ ብሎም በአካል ብቃት ላይ በማተኮር ሁሉን አቀፍ ስልጠና ይሰጣቸዋል ሲሉም ገልፀዋል።
በስልጠናው ማብቂያም ለ10 ወራት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በመሰማራት የበጎ ፍቃድ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እየሰጡ፤ ጎን ለጎን የየአካባቢውን ባህል እሴትና የህብረተሰቡን አኗኗር እንዲያውቁ በማድረግ፤ ሌላ አካባቢ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ ቤተሰባቸውን እንዲጎበኙት እንዲረዱት የሚያደርግ እድል የሚሰጥ መሆኑንም አስታውቅዋል።
እንዲሁም ከተለያየ ባህል ቋንቋ የመጡ ተማሪዎች እርስ በእርስ ማንነታቸውን ቋንቋቸውን አኗኗራቸውን እንዲለዋወጡና እንዲማማሩ በማድረግ በህዝቦች መካከል የነበረውን ወርቃማ ግንኙነት እና ውህድ ብሎም ኢትዮጵያዊ ለዛ ገብቷቸው በሚመለሱበት አካባቢ ይህን ስሜታቸውን እንዲያጋሩና እንዲያስፋፉ ማድረግ እንደሚያስችልም አብራርተዋል።
“መርሃ ግብሩ ታላቅ አገራዊ ተልእኮ ያዘለ መሆኑ ግልፅ ነው” ያሉት ሚኒስትሯ፥ በመሆኑም ለዚህ እንቅስቃሴ መሳካት መላው ኢትዮጵያዊ የተለመደ ትብብሩንና ድጋፉን ያደርግ ዘንድ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.